ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን ዐስቡ። አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል። እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ። ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። (ዕብራውያን 10፥32–35)
በዕብራውያን 10፥32-35 ያሉት ክርስቲያኖች ዋጋ የሚያስከፍል ፍቅር ምን እንደሚመስል በደንብ ያሳዩናል።
ነገሩ እንዲህ ነው፦ በክርስትና መጀመሪያ ላይ አንዳንዶቹ በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ሌሎቹ ደግሞ ከባድ ምርጫ ገጥሟቸው ነበር፦ “በድብቅ እየኖርን ‘ደኅንነታችንን’ እንጠብቅ? ወይስ ሕይወታችንንና ንብረታችንን ለአደጋ አጋልጠን እስር ቤት ያሉትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሄደን እንጠይቅ?” ታዲያ እነርሱ የፍቅርን መንገድ መርጠው ዋጋ ተቀበሉ።
“ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ” ይላቸዋል።
ታዲያ ግን ተሸናፊዎች ነበሩ ማለት ነው? በፍጹም! ንብረታቸውን አጥተው ደስታን አገኙ። ኪሳራውን በደስታ ተቀበሉ።
በአንድ በኩል ራሳቸውን ክደዋል፤ ይህም የሚያም እና ዋጋ የሚያስከፍል ነበር። በሌላ አንፃር ከተመለከትነው ግን የደስታን መንገድ መረጡ እንጂ አልከሰሩም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ የመቄዶንያ ሰዎች (በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፥1–9 ያሉት) ድሆችን ለመርዳት በተነሣሱበት መንገድ እንዲሁ፣ እነዚህ ክርስቲያኖችም ለእስር ቤት አገልግሎት ተነሣስተው ነበር። በእግዚአብሔር የነበራቸው ደስታ፣ በፍቅር ለሌሎች ተትረፈረፈ።
የራሳቸውን ሕይወት ተመልክተው “የእግዚአብሔር ቸርነት ከሕይወት ይሻላል” አሉ (መዝሙር 63፥3)።
ንብረታቸውንም ሁሉ ተመልክተው “የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት በሰማይ አለን” አሉ (ዕብራውያን 10፥34)።
ከዚያም እርስ በርሳቸው ተያዩ እና ምናልባትም የማርቲን ሉተርን ዐይነት ታላቅ መዝሙር የዘመሩ ይመስለኛል፦
ንብረት ይጥፋ፤ ዘመዶችም ይሂዱ፤
ይጥፋ ይሄም ሟች ሕይወት፤
ሰውነትን ቢገድሉም፣
ጸንቶ ይኖራል ቃሉ፤
ጸንቶ ይኖራል መንግሥቱ።
(A mighty fortress is our God, Martin Luther, 1529)