በጉን እንውደደው | መጋቢት 10

እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ። (ራእይ 5፥4)

ጸሎታችሁ እንደ መንግሥተ ሰማይ ሽታ አስባችሁት ታውቃላችሁ? የዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 5ን ስናነብ የምናገኘው ምስል ይህ ነው። ሕይወት በመንግሥተ ሰማይ ምን እንደምትመስል በጨረፍታ ያሳየናል።

በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 5 ላይ ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር በእጁ ጥቅል ይዞና በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ እናየዋለን። ጥቅሉ 7 ማኅተሞች ነበሩት፤ ከመከፈቱም በፊት ሰባቱ መነሣት ነበረባቸው።

የጥቅሉ መከፈት የታሪክን የመጨረሻ ቀናት የሚያሳይ ይመስለኛል፤ የማኅተሞቹ መነሣት ደግሞ ወደ እነዚያ ጊዜያት ስንጠጋ የምናልፍባቸውን ሁኔታዎች ያሳያል።

በመጀመሪያ ዮሐንስ ጥቅሉን ከፍቶ ማንበብ የሚችል ባለመኖሩ አለቀሰ (ራእይ 5፥4)። ከዚያ ግን ከሽማግሌዎቹ አንዱ እንዲህ አለ፤ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቶአል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” (ራእይ 5፥5)።

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱ፣ የቀረውን የድነት ታሪክ የመክፈት እና በዚያም ውስጥ ሕዝቦቹን በድል የመምራት መብት ተሰጥቶታል።

በቀጣዮ ቁጥር ላይ አንበሳው በበግ ተመስሏል፦ “የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ“ (ራእይ 5፥6)። ይህ እንዴት የሚያምር አገላለፅ ነው? የታረደ ቢመስልም ቆሞ ነበር!

ድሉን የተቀዳጀው ምንም እንኳ አንበሳ ቢሆንም ጠላቱ እንደ በግ እንዲያርደው በመፍቀድ ነበር!

እናም አሁን በጉ የመዳን ታሪክ የሆነውን ጥቅል ከእግዚአብሔር እጅ ወስዶ ለመክፈት ተፈቅዶለታል። ይህ ንጉሣዊ ድርጊት ከመሆኑ የተነሣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በፊቱ በአድናቆት ተደፉ።

በገናና ዕጣን የተሞሉት የወርቅ ሙዳዮች ምን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? (ራእይ 5፥8) “እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት“ ናቸው ይላል። ታዲያ ጸሎቶቻችን በእግዚአብሔር ዙፋን እና በበጉ ፊት መዓዛቸው የሚያውድ የመንግሥተ ሰማያት ሽታዎች አይደሉም?

ጸሎቴ ተሰብስቦ በመንግሥተ ሰማይ በክርስቶስ ፊት ለአምልኮ የሚቀርብ መሆኑን ሳስብ የበለጠ ለመጸለይ እበረታታለሁ።

ሁላችንም ኢየሱስን በጸሎታችን እናክብረው፤ ደግሞም እንውደደው። በድጋሚም የመንግሥተ ሰማይ የአምልኮ ስብስብ ጸሎታችንን እንደሚጣፍጥ የዕጣን ሽታ በታረደው በግ ፊት መልሶ እንደሚያቀርብልን እያሰብን ደስ ይበለን።