ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።
የዮሐንስ ወንጌል 10፥10
ይህንን የጥሞና ማጥኛ መጻፍ ልጀምር ስል፣ ማሪዮን ኒውስትረም የተባለች ሴት መሞቷ ተነገረኝ። ማሪዮን እና ባሏ ኤልመር በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በአባልነት የቆዩባቸው ዓመታት በጊዜው የነበሩ ሌሎች አባሎቻችን በሕይወት ከቆዩት ዓመታት ይረዝም ነበር። 87 ዓመቷ ነበር። ከባለቤቷ ለ64 ዓመታት በትዳር አብረው ቆይተዋል። ከኤልመር ጋር ባወራሁ ጊዜ በሕይወቱ ተስፋ እንዳይቆርጥ እና በጌታ እንዲበረታ ስነግረው፣ “እርሱ እውነተኛ ጓደኛ ሆኖልኛል” ብሎ መለሰልኝ። ክርስቲያኖች ሁሉ ወደ ሕይወታቸው መገባደጃ ሲደርሱ ልክ እንዲሁ፣ “ክርስቶስ እውነተኛ ጓደኛ ሆኖልኛል” ማለት እንዲችሉ ጸሎቴ ነው። የገና በዓል በደረሰ ጊዜ ሁሉ የእናቴን ሞት በማስታወስ ዓመታቱን እቆጥራለሁ። በ56 ዓመቷ በአውቶቡስ አደጋ በእስራኤል አገር ነበር የሞተችው። ቀኑ ታኅሳስ 7 ቀን 1967 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 16 ቀን 1974 ዓ.ም) ነበር። የዚያን ቀን አስከፊ ክስተት እስከ አሁን ድረስ በሚገርመኝ መንገድ በልቤ እውን ነው። ራሴን ካልከለከልኩት፣ በጣም በቀላሉ ዕንባዬ ይመጣል፤ ለምሳሌ፣ ልጆቼ ሳያውቋት መሞቷን ሳስብ። የገና በዓል ማግስት ቀበርናት። እንዴት ያለ ውድ የገና ቀን ነበር!
ብዙዎቻችሁ በዚህ ገና ያጣችሁትን ሰው በማስታወስ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ታዝናላችሁ። ስሜታችሁን አትዝጉበት። ይምጣ። ይሰማችሁ። አለዚያ ፍቅር ትርጉሙ ምን ሊሆን ነው? ለምንወዳቸው ሰዎች ያለን ፍቅር በሕይወትም ሆኑ በሞት ሊጋጋል ይገባል። ነገር ግን መራራ አትሁኑ። መራርነት እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ መንገድ ራስን ያጎሳቁላል። ኢየሱስ በገና ወደ እኛ የመጣው የዘለዓለም ሕይወት ይኖረን ዘንድ ነው። “እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ” (ዮሐንስ 10፥10)። ኤልመር እና ማሪዮን የዕድሜያቸውን የመጨረሻ ዓመታት የት እንደሚያሳልፉ ተነጋግረው ነበር። “ማርዮን እና እኔ የመጨረሻ ቤታችን ከጌታ ጋር እንደሚሆን ተስማምተን ነበር” ይላል ኤልመር።
የቤታችሁ ናፍቆት ዕረፍት ይነሣችኋል? በቤተሰባችን ውስጥ ለበዓላት የቤተ ዘመድ መገናኘት አለ። የበዓል ሰሞን ሲሆን ጠቅላላ ቤተሰባችን ከያለበት ተሰብስቦ ወደ ቤት ይመጣል። መሰባሰባችን በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው። ደስ የሚለን ዋነኛው ምክንያት ደግሞ፣ በማንነታችን ውስጥ የተቀበረ ለመጨረሻው የቤተ ዘመድ መገናኘት የታቀድን ሰዎች ስለሆንን ይመስለኛል። ሌሎች የቤተ ዘመድ መገናኘቶች ሁሉ ቅምሻዎች ናቸው። ቅምሻዎች ሁሉ ደግሞ መልካም ናቸው። መልካምነታቸው ግን ዋናውን እስካልተኩ ድረስ ብቻ ነው።
በዚህ ወቅት የምናገኛቸው ጣፋጭ ነገሮች የመጨረሻ እና ዘለዓለማዊ የሆነውን እና ሁሉን የሚያረካውን ዋነኛ ጣፋጭ የሚተኩ አይደሉም። አደራችሁን እንደ ምትክ እንዳትቆጥሯቸው። እያንዳንዱ ማጣት እና እያንዳንዱ ደስታ በመንግሥተ ሰማይ ለሚኖረው ዘለዓለማዊው የቤተ ዘመድ መገናኘት ልባችሁን ይምራ። ገና ይህ ካልሆነ ታዲያ ምንድን ነው? እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ማሪዮን ኒውስትረም፣ ሩት ፓይፐር፣ እናንተ እና እኔ ዛሬም ለዘለዓለምም ሕይወት እንዲኖረን መጥቶልናል! በዚህ የገና ሰሞን ከዘለዓለማዊው ምንጭ በመጠጣት ዛሬያችሁ የበለጸገ እና ጥልቅ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው አድርጉ። ደርሷል፤ እጅግ ቅርብ ነው።