ሕይወት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተንጠልጥሏል | መስከረም 19

እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ በምትወርሷትም ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ። (ዘዳግም 32፥46-47)

የእግዚአብሔር ቃል ዋጋ ቢስ አይደለም፤ የሕይወት እና የሞት ጉዳይ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ ዋጋ ቢስ ወይም እንደ ባዶ ቃላት ካያችኋቸው፣ ለሕይወት ጀርባ ሰጥታችኋል።

የምድር ሕይወታችን እንኳ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተንጠለጠለ ነው፤ ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው በቃሉ ነው (መዝሙር 33፥6ዕብራውያን 11፥3)። “በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል” (ዕብራውያን 1፥3)።

መንፈሳዊ ሕይወታችንም የሚጀምረው በእግዚአብሔር ቃል ነው፦ “በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን” (ያዕቆብ 1፥18)። ዳግመኛ የተወለዳችሁት… ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር፣ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት… ነው (1ኛ ጴጥሮስ 1፥23)።

በእግዚአብሔር ቃል መኖር መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ቃል መኖራችንንም እንቀጥላለን፦ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴዎስ 4፥4ዘዳግም 8፥3)።

ስለዚህ ምድራዊው ሕይወታችን የተፈጠረውና የሚደገፈው በእግዚአብሔር ቃል ነው። መንፈሳዊ ሕይወታችንም በእግዚአብሔር ቃል ሕያው ሆኖ፣ ጸንቶ ይኖራል። የእግዚአብሔር ቃል ሕይወት ሰጪ ኃይል ያለው መሆኑን የሚያስመስክሩ ስንት ታሪኮች ይኖሩ ይሆን!?

በርግጥም ቅዱሳት መጽሐፍት ለእናንተ “እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤” ሕይወታችሁ ናቸው። የደስታ ሁሉ መሠረት ነው። ከመኖር የበለጠ መሠረታዊ ነገር የለም፤ የእኛ መፈጠር ሆነ ጸንተን መኖራችንም የቃሉ ውጤት ነው።

ይህ ሁሉ የሆነው በእግዚአብሔር ኅያል ቃል ነው። በዚያው ኅይል፣ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጀምር እና ጸንቶ እንዲቀጥል በቅዱሳት መጻሕፍት በኩል ተናግሯል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ባዶ ቃል አይደለም። ነገር ግን ቃሉ ሕይወታችን፣ የደስታችን መሠረትና ምንጭ ነው!