የአብርሃም ሊንከን መግቦት | የካቲት 13

የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም! (ሮሜ 11፥33)

የካቲት 6 ቀን 1801 የተወለደው አብርሃም ሊንከን፣ እስከ ዕድሜው 40ዎቹ ድረስ ስለ ኀይማኖት ነገር ተጠራጣሪና አንዳንዴም ነቃፊ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ መካከል፣ በግሉ እና በሐገር ላይ መከራ ሲደርስ አብርሃም ሊንከን የእግዚአብሔርን እውነታ ከመግፋት ይልቅ እንዴት ወደ እግዚአብሔር እንደተሳበ ማየት በጣም የሚያስገርም ነገር ነው።

በ1854 ሊንከን 53 ዓመቱ እያለ፣ ዊሊ የተባለው የ11 ዓመት ልጁ ይሞታል።  የሊንከን ሚስት “የአዲስ ዘመን መንገዶችን (New Age)” መንገዶችን በመፈለግ ሐዘኗን ለመቋቋም ሞክራለች። አብርሃም ሊንከን ግን በዋሽንግተን የኒው ዮርክ ጎዳና የፕሪስቢቴሪያን ቤተክርስቲያን ፓስተር ወደ ነበረው ፊንሃስ ገርሊ ዘወር አለ።

ከበርካታ ረጃጅም ውይይቶች እና ክርክሮች በኋላ፣ አብርሃም ሊንከን ክርስቶስን ወደማመን እንደመጣ ይህ ሰባኪ ይናገራል። አብርሃምም “ሌላ የምሄድበት ቦታ እንዳልነበረኝ በመረዳት፣ ብዙ ጊዜ በጉልበቶቼ ወድቄአለሁ” ሲል ተናዝዟል።

በተመሳሳይ ደግሞ የሞቱ እና የቆሰሉ ወታደሮች አሰቃቂነት በየዕለቱ ያስጨንቀው ነበር። በዋሽንግተን ውስጥ ለቁስለኞች ብቻ የሚውሉ 50 ሆስፒታሎች ነበሩ። የካፒቶል አዳራሽ ሁለት ሺ የቁስለኛ ወታደሮች ቃሬዛን ይዞ ነበር።

በእነዚህ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች ውስጥ በቀን የ50 ወታደሮች ሞት የተለመደ ነበር። ይህ ሁሉ ሊንከንን ወደ እግዚአብሔር መግቦት መራው። “ዓለምን የፈጠረው እርሱ ራሱ አሁንም ያስተዳድረዋል ብለን ከማመን ውጪ ምንም አማራጭ የለንም” ይላል።

ከመገደሉ ከአንድ ወር በፊት፣ በሁለተኛው የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ከእግዚአብሔር መግቦት ጋር በተያያዘ ስለ እርስ በእርስ ጦርነቱ የተናገረው ንግግሩ በጣም ታዋቂ ነበር። በጊዜው ተፋላሚ ከነበሩት ሁለቱ ጎራዎች መካከል፣ እግዚአብሔርን የአንዱ ደጋፊ አለማድረጉ የሚደንቅ ነገር ነው። እግዚአብሔር የዩንየን ወይም የኮንፌደሬቶች ዓላማ ደጋፊ ያልሆነ እና የራሱ ዓላማ ያለው፣ ወገንተኛ ሆኖ ኀጢአትን ቸል የማይል አምላክ ነው። አብርሃም ሊንከን እንዲህ ሲል ይናገራል፦

“ይህ አሰቃቂ የጦርነት ጊዜ በፍጥነት እንደሚያልፍ ተስፋ እናደርጋለን፤ እንዲያልፍም አጥብቀንም እንጸልያለን …

ነገር ግን እግዚአብሔር ጦርነቱ እንዲቀጥል ከፈቀደ፣ በባሮች የሁለት መቶ ዓመት ድካም የተከማቸው ሀብት ሁሉ እስኪወድም እና በአሰቃቂ ግርፊያ የፈሰሰው እንያንዳንዱ የደም ጠብታ በተበዳዩ በተመዘዘ ሰይፍ እስኪከፈል ድረስ እንዲቀጥል እግዚአብሔር ከወሰነ፣ ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ‘የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ጽድቅ ናቸው’ ተብሎ እንደተነገረ ሁሉ፣ አሁንም መነገር አለበት።”

በበሸታ፣ በመከራ፣ በኪሳራ፣ በአደጋ እና በጥልቅ ሐዘን ለምትሠቃዩ ሁሉ፣ የምታልፉበት መንገድ ለአብርሃም ሊንከን እንደሆነለት፣ ዕጣ ፈንታችሁ ላይ ከማሳበብ ይልቅ፣ ማለቂያ በሌለው የእግዚአብሔር ጥበብ፣ ፍቅር እና እንክብካቤ ላይ ከልብ ወደመደገፍ እንዲመራችሁ እጸልያለሁ።