ለደስታችሁ ወደ ኢየሱስ ተመልከቱ | መጋቢት 5

“ለመታየት ሲሉ የሚያደርጉትን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋሉ፤ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የቀሚሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ። በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ ይወዳሉ። እንዲሁም በገበያ መካከል ሰላምታ መቀበልንና በሰዎች አንደበት ‘መምህር’ ተብለው መጠራትን ይሻሉ።” (ማቴዎስ 23፥5-7)

ለራሳችን ያለን ግምት ሁልጊዜም ስለ ራሳችን ከፍ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ያስገድደናል። ደስታችን የሚመነጨው በራሳችን ብቁ እንደሆንን በማሰብ ከሆነ፣ ሌሎች ብቁነታችንን እስካላዩልንና ዕውቅና እስካልሰጡን ድረስ አንረካም።

ኢየሱስ በማቴዎስ 23፥5 ስለ ጻፎች እና ፈሪሳውያን የተናገረውም ይህንን ነው፤ “ለመታየት ሲሉ የሚያደርጉትን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋሉ።”

ይህ በእውነት አስገራሚ ነው። በራሴ ብቁ ነኝ የሚለው የትዕቢተኛ ሰዎች አመለካከት፣ የሌሎችን ዕውቅና ከመፈለግ አያድናቸውም፤ “ብቁ” ማለት ይሄ ነው። ነገር ግን በዚህ ዐይነቱ ብቁነት ውስጥ ባዶነት አለ።

ማንነታችን በራሱ እንዲረካ ወይም እንዲተማመን አልተፈጠረም። መቼም ቢሆን በራሱ ብቁ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም እኛ እግዚአብሔር አይደለንም፤ በእርሱ አምሳል ተፈጠርን እንጂ። እናም እንደ እርሱ እንድንመስል የሚያደርገን ራሳችንን መቻላችን አይደለም። እኛ ጥላዎች እና የገደል ማሚቶች ነን፤ ስለዚህ ሁልጊዜም በነፍሳችን ውስጥ በራሳችን እንዳንተማመን የሚያደርግ ባዶነት አለ።

የሌሎችን ሙገሳ እና ዕውቅና መፈለጋችን፣ ሁሌም የትምክህታችንን ውድቀትና በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ እምነት ማጣታችንን ያሳያል። ከሰው ክብር መፈለጋችን የሚያሳድረውን ተጽእኖ ኢየሱስ አይቶት ነበር። በዮሐንስ 5፥44 “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትፈልጉ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” ሲል ተናግሯል። መልሱ አትችሉም ነው። ከሌሎች ክብርን መፈለግ፣ እምነትን የማይቻል ያደርገዋል። ለምን?

ምክንያቱም እምነት ከራስ ይልቅ ወደ እግዚአብሔር መመልከት ነው። ምክንያቱም እምነት እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ በሆነልን ሁሉ መርካት ነው። እናም አሁን የሌሎችን ክብር በማግኘት ውስጥ እርካታን የምትፈልጉ ከሆነ ከኢየሱስ ትርቃላችሁ። እርሱ ባሕሪው እንደዚህ አይደለም፤ ለአባቱ ክብር የሚኖር ነው። እኛም እንደዚያው እንድናደርግ ይፈልጋል።

ነገር ግን ከማንነታችሁ ውስጥ እርካታን መፈለግ ከተዋችሁ (ንስሓ ከገባችሁ) እና ወደ ኢየሱስ ተመልሳችሁ እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ በሆነልን ሁሉ በእምነት መርካት ከጀመራችሁ፣ ያን ጊዜ ባዶነታችሁ በሙላት ይተካል፤ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል” (ዮሐንስ 4፥14)።