እርስ በርሳችሁ በደስታ ተዋደዱ | ጥቅምት 29

ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን? (ሚክያስ 6፥8)

አንድን ሰው “አንተ በመደሰትህ ምክንያት ያኛው ሰውዬ ይደሰታል” ብንለው መጥፎ ስሜት አይሰማውም። ለሰው መልካም የማደርገው ደስ ስለሚያሰኘኝ ነው ብል፣ በራስ ወዳድነት የሚከሰኝ ሰው አይኖርም። በፍቅር የተሞሉ ተግባራት በብስጭት የሚደረጉ አይደሉም።

ከብስጭት ወይም ግድ የለሽነት ይልቅ ደስታ የተሻለ አማራጭ ነው። እውነተኛው የፍቅር ልብ፣ ደግነት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ደግነትን ይወዳል (ሚክያስ 6፥8)። ክርስቲያን ሄዶኒዝም ይህንን እውነት ከግምት ውስጥ እንድናስገባ ይገፋፋናል።

“እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደ ምንወድ በዚህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል” (1ኛ ዮሐንስ 5፥ 2–4)።

እነዚህን ዐረፍተ ነገሮች በተገላቢጦሽ አንብቡና የሃሳብ ፍሰቱን አስተውሉ። በመጀመሪያ፣ ከእግዚአብሔር መወለድ ዓለምን የሚያሸንፍ ኅይልን ይሰጣል። ይህ “የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሸክም አይደሉም” ለሚለው መግለጫ እንደ መሰረት ወይም ማስረጃ ተሰጥቷል (“ምክንያቱም” የሚለውን ቃል አስተውሉ)።

ስለዚህ ከእግዚአብሔር መወለድ ዓለማዊ ምኞቶቻችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንድናስገዛ ኅይልን ይሰጣል። አሁን ትእዛዛቱ “ሸክም” አይደሉም፤ ነገር ግን የልባችን ፍላጎትና ደስታ ናቸው። የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነው፤ ትዕዛዛቶቹ እንድንፈጽም ብቻ ሳይሆን ቀንበር እንዳይሆኑብን ኅይልን ሰጥቶናል።

በመቀጠልም በቁጥር 2 ላይ፦ “ለእግዚአብሔር ልጆች ያለን ፍቅር እውነተኛነት ማስረጃ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው” ተብሏል። ይህ ለእግዚአብሔር ልጆች ስላለን ፍቅር ምን ያስተምረናል?

እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ፈቃዱን በሸክም ስሜት ከማድረግ ይልቅ በደስታ ማድረግ እስከሆነ ድረስ፥ ደግሞም ለእግዚአብሔር ልጆች ያለን ፍቅር እውነተኛነት መለኪያ እግዚአብሔርን መውደድ እንደሆነ ካየን፣ ስለዚህ፥ ለእግዚአብሔር ልጆች ያለን ፍቅር ደግሞ በቸልተኝነት ሳይሆን በደስታ ሊሆን ይገባል።

ክርስቲያን ሄዶኒዝም በፍቅር ድርጊት ላይ የጸና አቋም አለው፤ እንዲሁ ወደ ቸልተኛ መታዘዝ ሳይሆን ደስታን ወደተሞላ መታዘዝ ይገፋፋናል።