የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና። (ኤፌሶን 5፥29-30)
የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር እንዳትስቱት፣ “እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና።” ጳውሎስ ሁለት ቁጥሮች ከፍ ብሎ ያለውንም አስታውሱ፦ “ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው።” ኢየሱስ እንዴት የራሱን ደስታ የሕዝቡን ቅድስናና ውበት በመፈለግ ውስጥ እንደሚያገኘው በሁለት መንገዶች ጳውሎስ ይነግረናል።
በክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው አንድነት እጅግ ከመጥበቁና አንድ አካል ከመሆኑ የተነሣ፣ ለእርሷ የሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ለራሱ እንደሚያደርገው ነው። ስለዚህ የዚህ ጥቅስ ዋና መልእክት ክርስቶስ የራሱን ደስታ ለማግኘት ሲል ሙሽራውን የሚመግባት፣ የሚያነፃት እና የሚቀድሳት መሆኑ ነው።
በአንዳንድ ሰዎች የፍቅር ፍቺ መሰረት ይህ ፍቅር ሊሆን አይችልም፤ ፍቅር ከራስ ፍላጎት የነፃ መሆን አለበት ይላሉ፤ በተለይ የክርስቶስ ፍቅር፤ በተለይ የመስቀሉ ፍቅር። ይህ ዐይነት አተያይ ከዚህ ጥቅስ ጋር ሲታረቅ አይቼ አላውቅም።
ነገር ግን ክርስቶስ ለሙሽራው የሚያደርገውን ይህንን ድርጊት፣ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ፍቅር ይለዋል፦ “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት… እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ…” ይለናል (ኤፌሶን 5፥25)። ታዲያ የፍቅርን ፍቺ ከሞራልና ፍልስፍና ትምህርት ከመውስድ ይልቅ መጽሐፉ እንዲነግረን ለምን አንፈቅድለትም? በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ ፍቅር ማለት ክርስቶስ በወደደው ውስጥ ደስታውን መፈለጉ ነው።
የራስ ፍላጎትን ከፍቅር መለየት አይቻልም፤ ምክንያቱም የራስን መፈለግ ከራስ ወዳድነት የተለየ ስለሆነ ነው። ራስ ወዳድ መሆን የግል ደስታን ለሌሎች ሳይጨነቁ ማሳደድ ነው።
እንደ ክርስቶስ ያለ ፍቅር ደስታውን በሌሎች መደሰት ውስጥ ይፈልጋል። በሚወዳቸው ሰዎች ደስታ ውስጥ ሙሉ ደስተኛ ለመሆንም ለእነርሱ እስከ መሰቃየት እና እስከ መሞት ይደርሳል።
ክርስቶስ የወደደን በዚህ መንገድ ነው፤ እርስ በርስ እንድንዋደድ የሚጠይቀንም እንዲሁ ነው።