ሰይጣንን ሽንፈቱን እንዲያውቅ አድርጉት | ሚያዚያ 9

ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። (ያዕቆብ 4፥7)

ባለንበት ዘመን ሰይጣን የበለጠ እውን እየሆነ እና በግልጽ እየሰራ በመጣ ቁጥር፣ የክርስቶስም ድል በእርሱ ለሚታመኑት የበለጠ ውብ እና ውድ እየሆነ ይሄዳል።

ክርስቶስ ሞቶ በተነሣ ጊዜ ሰይጣን ጨርሶ እንደተሸነፈ አዲስ ኪዳን ያስተምረናል። በእርግጥ ውስን የሆነ የነፃነት ጊዜ ተሰጥቶታል፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያለው ኃይሉ ተሰብሯል። ፈጽሞ መጥፋቱ ደግሞ የተረጋገጠ ነው።

  • “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው።” (1ኛ ዮሐንስ 3፥8)
  • “ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ [ክርስቶስ] ራሱ ደግሞ ያንኑ [ሥጋና ደም] ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው።” (ዕብራውያን 2፥14)
  • “[እግዚአብሔር] የአለቆችንና የባለ ሥልጣናትንም ማዕረግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።” (ቈላስይስ 2፥15)

በሌላ አነጋገር፣ ወሳኝ የሆነው ጥቃት የተደረገው በቀራንዮ ላይ ነው ማለት ነው። እናም ደግሞ አንድ ቀን፣ ለሰይጣን የተገደበለት የነጻነት ጊዜ ሲያበቃ፣ ራእይ 20፥10 እንደሚናገረው ይሆናል፦ “ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።”

ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምንከተል ሰዎች ይህ ምን ማለት ነው?

  •  “ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም።” (ሮሜ 8፥1)
  •  “እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው።” (ሮሜ 8፥33)
  • “ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት፣ ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።” (ሮሜ 8፥38–39)
  • “በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል።” (1ኛ ዮሐንስ 4፥4)
  • “እነርሱም [ጻድቃን] በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሡት።” (ራእይ 12፥11)

ስለዚህ፣ “ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል!” በእርግጥም ተሸንፏል፤ እኛ ደግሞ ድልን ተጎናጽፈናል። አሁን ከእኛ የሚጠበቀው በዚያ ድል ውስጥ መኖርና፣ ሠይጣንን ደግሞ ሽንፈቱን እንዲያውቅ ማድረግ ነው።