ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቊር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። (ኤፌሶን 6፥16–17)
ዕድሜዬ መግፋቱ ሲያሳስበኝ፣ አለማመንን በዚህ ቃል እዋጋለሁ፦ “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ” (ኢሳይያስ 46፥4)።
ስለ መሞት ስጨነቅ አለማመንን በዚህ ቃል እዋጋለሁ፦ “ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን። ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአል፤ በሕይወትም ተነሥቶአል” (ሮሜ 14፥7–9)።
ከእምነት እንደምጎድል እና ከእግዚአብሔር እጅ እንዳልወድቅ ስሠጋ፣ አለማመንን በዚህ የተስፋ ቃል እዋጋለሁ፦ “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እ ርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ” (ፊልጵስዩስ 1፥6)። “ስለ እነርሱ እየማለደ ሁል ጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” (ዕብራውያን 7፥25)።
የክተት ጥሪዬን እንድትቀበሉ እጋብዛችኋለሁ! ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይሆን፣ ከራሳችን አለማመን ጋር ጦርነት እንግጠም። በእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት አለማመን የጭንቀት ሥር ነው፤ ይህ ደግሞ ለሌሎች ኅጢአቶች ሥር መሠረት ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን 6፥17 የመንፈስ ሰይፍ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብሏል። የሰይጣንን ማታለያዎች የምንከላከልበት ጋሻ እምነት ነው (ቁጥር 16)። ይኽውም በእግዚአብሔር ቃል ያለ እምነት ነው። ስለዚህ ጋሻውን በግራ እጃችን፣ ሰይፉን ደግሞ በቀኝ እጃችን ይዘን መልካሙን የእምነት ገድል እንጋደል።
መጽሐፍ ቅዱስን አንሡ! ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ጠይቁ! የተሰጡትን የተስፋ ቃሎች በልባችሁ አኑሩ! መልካሙን ውጊያ ተዋጉ! ይኽውም ወደ ፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ በእምነት እንድትኖሩ ነው።