ኢየሱስ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን ከቀድሞው እንደሚበልጥ ሁሉ፣ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፤ ይህም የተመሠረተው በተሻለ የተስፋ ቃል ላይ ነው።
ዕብራውያን 8፥6
ዕብራውያን 8፥6 እንደሚነግረን ክርስቶስ የአዲሱ ኪዳን አማላጅ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በማይገረሰስ መልኩ በአዲሱ ኪዳን ደም አማካኝነት ለእኛ ተገዝቶልናል፣ ተጠብቆልናል (ሉቃስ 22፥20፤ ዕብራውያን 13፥20)።
ይህ ማለት እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን የተስፋ ቃሉ መሠረት ውስጣዊ የሆነ ሥር ነቀል ለውጥ በክርስቶስ መንፈስ በኩል አስገኝቶልናል ማለት ነው።
በተጨማሪም ደግሞ እግዚአብሔር ይህንን ውስጣዊ መለወጥ በእኛ ውስጥ የሚሠራው በእምነት ነው። ይህም እምነት እግዚአብሔር በክርስቶስ ስለ እኛ የሠራውን እና የሆነውን ሁሉ በማመን የሚገኝ ነው።
አዲሱ ኪዳን በክርስቶስ ደም ተገዝቶ፣ በክርስቶስ መንፈስ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጎ፣ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ደግሞ ወደ እኛ ይተላለፋል።
ክርስቶስ የአዲሱ ኪዳን አማላጅ ሆኖ ሲሠራ ለመመልከት ወሳኙ ቦታ ዕብራውያን 13፥20-21 ነው፦
“በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።”
“…በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ…” የሚሉት ቃላት የሚያብራሩት እግዚአብሔር ከአዲሱ ኪዳን ጋር በተስማማ መልኩ ሕጉን በልባችን ሲጽፍ ምን እንደሚፈጠር ነው። “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል” የሚሉት ቃላት ደግሞ የሚያብራሩት የዚህ አስገራሚ የሉዓላዊ ጸጋ ሥራ አማላጅ ኢየሱስ መሆኑን ነው።
ስለዚህም የገና ዋና ትርጉም እግዚአብሔር ጥላውን በትክክለኛው ነገር መተካቱ ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ትክክለኛ ነገር ወስዶ ለሕዝቡ ተጨባጭ እውነት ማድረጉም ጭምር ነው። በልባችን ላይ ይጽፈዋል። የዘለዓለም ሕይወትን እና መለወጥን የገና ስጦታ አድርጎ ሲሰጠን፣ እንዲያው እንደታሸገ በራሳችን አቅም እንድናነሣው ከገና ዛፉ ሥር አይደለም ያስቀመጠው። አንስቶ በልባችሁ እና በአእምሯችሁ ካጸናው በኋላ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችሁን የሚያረጋግጥላችሁ ማኅተም ይሰጣችኋል።