ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር

ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ እንዲሆን የመረጥኩት “ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር” የሚልን ዐረፍተ ነገር ነው። በዚህም ርዕስ ውስጥ ልናስተውለው የሚገባው ወሳኙ ቃል፣ “” የሚለውን ነው፤ እግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር። ምክንያቱም “ለ” የሚለው ቃል፣ በእግዚአብሔር እና በትዳር መካከል ያለውን ትክክለኛ ቅደም ተከተል ስለሚያሳይ ነው።

ቅደም ተከተሉም ግልጽ ነው፦ እግዚአብሔር የመጨረሻ ግብ ነው፤ ትዳር ግን አይደለም። እግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ የሆነ እውነታ ነው፤ ትዳር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጻጸር ምንም ነው።

ትዳር ለምን ተፈጠረ?

ይህንን ርዕስ ከራሴ አላመጣሁትም፤ ትዳር ለምን ተፈጠረ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስል የመረጥኩት ነው። ”ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር” የሚለው ርዕስ፣ “ትዳር ለምን ተፈጠረ?” የሚለውን ጥያቄ ለእግዚአብሔር ክብር መሆኑን በማሳየት ይመልሳል። ይህም ደግሞ ለሌላ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ነው። የተፈጠረው ነገር ሁሉ ለምን ተፈጠረ? ለምንስ ይኖራል? እናንተስ ለምን ተፈጠራችሁ? ለምንስ ነው የግብረ ሥጋ ግንኙነት የተፈጠረው? ይህ ዓለም፣ ፀሓይና ጨረቃስ ለምን ተፈጠሩ? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው መልስ፣ “ሁሉም ነገር የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው” የሚል ነው።

ይህም ማለት የመኖራቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበት እና ታላቅነት ለማጉላት ነው። የመፈጠራችን ዓላማ ይህ ነው። ትዳር የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትና ታላቅነት ለማጉላት ተፈጠረ እንጂ፣ እግዚአብሔር ትዳርን ለማጉላት አይኖርም። ይህንን ቅደም ተከተል፣ ግልጽ በሆነ መልኩ እስካላየነው፣ እስካልተረዳነው፣ እስካላከበርነውና እስካላጣጣምነው ድረስ፣ ትዳር የእግዚአብሔርን ክብር፣ ውበት፣ እውነትና ታላቅነት በፍጹም አጉልቶ ማሳየት አይችልም።

ማይክሮስኮፕ ሳይሆን፣ ቴሌስኮ

ታዲያ የተፈጠሩት የእግዚአብሔርን ክብር ለማጉላት ነው ስል፣ ማይክሮስኮፕ አንድን ነገር በሚያጎላበት መልኩ ሳይሆን፣ እንደ ቴሌስኮፕ ማለቴ ነው። ማይክሮስኮፕ ጥቃቅን ነገሮችን ትልቅ በማድረግ ሲያጎላ፣ ቴሌስኮፕ ግን ታላቅነታቸው ሊታሰብ የማይቻልን ነገሮች በማቅረብ ምን እንደሆኑ ያሳየናል። እግዚአብሔርን በማይክሮስኮፕ ማጉላት መሳደብ ነው፤ በቴሌስኮፕ ማጉላት ግን አምልኮ ነው።

ማይክሮስኮፕ ከእውነታው ዓለም በማራቅ የነገሮችን መጠን እጅግ አግዝፎ ሲያሳየን፣ ቴሌስኮፕ ግን የነገሮችን መጠን ወደ እውነታ ያመጣል። ስለዚህ ትዳርን ጨምሮ፣ እናንተም፣ ዓለምም፣ ፀሓይም፣ ጨረቃም፣ እንስሳትም፣ እፅዋትም፣ ከጥቃቅን ነገሮችም አንስቶ እስከ አጽናፈ ዓለሙ ድረስ፣ ሁሉም ነገሮች የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትና ታላቅነት እንዲያጎሉ ተፈጥረዋል። ይህንንም ስል የሰዎችን አእምሮ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር መገለጥ እንዲመሩ ተፈጥረዋል ማለቴ ነው።

እግዚአብሔር ሊገመት በማይችል መልኩ እጅግ ታላቅ፣ እጅግ ውድ እና እጅግ ውብ ነው። ወደ መኖር የመጣ የትኛውም ነገር ይህንን እውነት ለማላቅ የተፈጠረ ነው።

መዝሙር 145፥3 እንዲህ ይላል፦

“እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም።”

ኢሳይያስ 43፥6-7 ደግሞ እንዲህ ይላል፦

“ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀውትንና የሠራሁትን አምጡ።”

የተፈጠርነው የእግዚአብሔርን ክብር ለማንጸባረቅ መሆኑ ግልጽ ነው።

ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ

የሮሜ መጽሐፍ ታላቅ የሆነ መጽሐፍ ነው። ጳውሎስ በመጽሐፉ መጨረሻ አሳቡን ሲጠቀልል እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም! ‘የጌታን ልብ ያወቀ ማነው? አማካሪውስ የነበረ ማን ነው?’ ‘እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣ ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው? ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን” (ሮሜ 11፥33-36)።

ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነው። ስለዚህ የሁሉ ነገር ምንጭ እግዚአብሔር ነው፤ በእርሱም ተጠብቆ ይኖራል፤ ደግሞም ለእርሱ ተፈጥሯል ማለት ነው። በቆላስይስ 1፥16 ላይ፣ ስለ ክርስቶስ የተነገረውን ተመልከቱ፤ “ሁሉ ነገር በእርሱ (በክርስቶስ) ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”

ይህ እጅግ ግልጽ የሆነ ነገር ነው። ሁሉም ነገር የተፈጠረው ለክርስቶስ ነው። ታዲያ አንዳንድ የልጆች መጽሐፍት እንደሚያደርጉት፣ “ለክርስቶስ” የሚለውን ሐረግ፣ “ለእርሱ ጥቅም” ወይም “እርሱ እንዲኖር” ወይም “እርሱ እንዲሻሻል” ብላችሁ ከተረጎማችሁ፣ ወዮላችሁ! ምክንያቱም በሌላ አነጋገር፣ “ምስኪኑ እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙን የፈጠረው፣ ብቸኛ ስለነበረና ጓደኛ ስላስፈለገው ነው” እያላችሁ ነው። ይህ ደግሞ ያለ ምንም ማጋነን እግዚአብሔርን መስደብ ነው።

ስለዚህ “ለክርስቶስ” ማለት “ለእርሱ ጥቅም” ወይም “እርሱ እንዲሻሻል” ማለት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን እውነት፣ ታላቅነትና ክብር በሰዎች ዘንድ አጉልቶ ለማሳየት ማለት ነው። “ሁሉ ነገር ለክርስቶስ ነው” ማለት፣ ሁሉም ነገር የተፈጠረው የክርስቶስን ክብር በሰዎች ሕይወት ውስጥ በማጉላት፣ ማንነቱን እዲያዩና እንዲያውቁ ለማድረግ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ እርሱ የክብሩ ነጸብራቅ ነው።

“በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረውም ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም” (ዮሐንስ 1፥1-3)።

ስለ ትዳር ያለን ምልከታ ሊቀዳ የሚገባው ከዚህ መሠረታዊ እውነት ነው። ይህንን በተሳሳተ መንገድ ተረድተነው ከሆነ፣ ሁሉም ነገር ላይ እንሳሳታለን። በትክክል በአእምሮአችን እና በልባችን ከተረዳነው ግን፣ ትዳራችን ለተፈጠረለት ዓላማ መዋል ይችላል። ይህም ሲሆን የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበት እና ታላቅነት ይገልጣል።

የስብከታችን ማዕከል

ታዲያ ይህ በጣም ግልጽ ወደ ሆነ ድምዳሜ ይመራናል። ትዳርን በዚህ መንገድ የምንመለከተው ከሆነ፣ እንዲሁም በዓለምና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተፈጠረለት ዓላማ እንዲውል የምንፈልግ ከሆነ፣ ደግሞም የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትና ታላቅነት እንዲያጎላ የምንፈልግ ከሆነ፣ ከትዳር ይልቅ አብልጠን ስለ እግዚአብሔር ልንሰብክ ይገባል።

አሁን ላይ በትዳር የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ወጣቶች፣ የእጮኝነት ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ማንነት፣ ባሕርይ እና አሠራር ላይ ተመሥርተው አይቃኙትም። በዚህችም ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርን ማየት ከባድ ሆኗል። በሰርግ ድግሶች ላይም አይጋበዝም። በሚያስደነግጥ መልኩ ከሁሉም ነገር ተባሯል። ባህላችንን ብቻ እንኳ ማየት ልብን ይሰብራል። እግዚአብሔርን ረስተነዋል።

ጠዋት ከእንቅልፋቹ ነቅታችሁ ቴሌቭዥናችሁን ስትከፍቱ፣ ከተደረደሩት የዜና ርዕሶች መካከል ስለ እግዚአብሔር የሚያወራ ነገር ባለማየታችሁ ትደነግጣላችሁን? በፍጹም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ችላ ካለ ባህል ጋር ተላምደናል። እግዚአብሔርን ከገፉ ማስታወቂያዎች፣ ጋዜጣዎችና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጋር ተሰፍተናል። ሊያስደነግጠን የሚገባው ነገር አያስደነግጠንም።

ሲሆን ሲሆን በዓለም ላይ በግልጽ የእግዚአብሔር መገኘት አለመታየቱ እጅግ ሊያስደንቀን ይገባ ነበር። ምክንያቱም በዘላለም ቁጣው ምድርን ከፀሓይና ጨረቃ ጋር አጣብቆ ሊጨፈልቀን ሲገባ፣ እኛ ግን ዛሬም እየተነፈስን አለን። በሕይወት መቆየታችን ብቻ እጅግ ይገርማል። ነገ ጠዋት የመነሳታችንም እውነታ የማይታመን ነው። እግዚአብሔር ለጻድቁም ለኀጢአተኛውም ፀሓይን ያወጣል። ይህንን እውነት ቆም ብላችሁ በማሰብ ተገረሙ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ወጣቶቻችን ስለ እግዚአብሔር ያላቸው መረዳት፣ ትልቅ ሊሆን ሲገባው እጅግ ያነሰ ነው። ግልጽ ከመሆን ይልቅ የደበዘዘ፣ ማዕከል ሊሆን ሲገባው ዳር የያዘ፣ እንዲሁም ሁሉን በያኒ ከመሆን ይልቅ አቅመ ቢስ የሆነ ነው። ከዚህም የተነሣ ጥንዶች ወደ ትዳር ሲመጡ፣ “ትዳርን ለእግዚአብሔር ክብር መኖር” የሚለውን አሳብ፣ በአፋቸው ቢሉትም ትርጉም የለሽ ግን ይሆንባቸዋል።

የእግዚአብሔር ክብር ስንል ምን ማለታችን ነው?

ስለዚህ ትዳር ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲውል ከተፈለገ፣ በቅድሚያ ስለ ትዳር ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር ልንናገር ይገባል። ነገር ግን መድረኮቻችን የእግዚአብሔርን ክብር የሚያስተጋቡ አይደሉም። ይህንን ግን ቢያደርጉ የሰዎችን አእምሮ በእነዚህ እውነቶች መሙላት ይችላሉ።

  • ከአእምሮ የሚያልፈው ጅማሬና ፍጻሜ የሌለው አምላክ የዘላለማዊነቱ ክብር
  • በዓለማችን ታላቅ የሚባለውን ቤተ መጽሐፍት እንደ ኢምንት የሚያስቆጥረውን የዕውቀቱ ክብር
  • በሰው ልጅ ሊመከር የማይቻለው የጥበቡ ክብር
  • በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች ከእርሱ ፈቃድ ውጪ አጋንንት እንኳ ምንም ማድረግ የማያስችላቸው የሥልጣኑ ክብር
  • ከፈቃዱ ውጪ በደን ውስጥ ያለች አንዲት ቅጠል እንኳ መሬት የማትወድቅበት፣ አንዲትም ጸጉር ልትሸብት የማትችልበት የመግቦቱ ክብር
  • ከጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ጀምሮ አጽናፈ ዓለሙን ሁሉ ደግፎ የያዘው የቃሉ ክብር
  • በውሃ ላይ የሚራመደው፣ ለምጻሞችን የሚያነጻው፣ ሽባዎችን የሚፈውሰው፣ የዕውሮችን ዐይን የሚያበራው፣ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ የሚያደርገው፣ በቃሉ ወጀብን ዝም የሚያሰኘው፣ ሙታንንም የሚያስነሣው የኀይሉ ክብር
  • ኀጢአትን ሊሠራ፣ ክፉንም ሊያስብ ፈጽሞ የማይቻለው የንጽሕናው ክብር
  • ቃሉን ፈጽሞ የማያጥፈው የታማኝነቱ ክብር
  • በአጽናፈ ዓለም ላይ ያሉትን ድርጊቶች ሁሉ በመስቀሉ የሚምር፣ አልያም በሲኦል የሚቀጣው የፍትሐዊነቱ ክብር፤ (በመጨረሻውም ቀን ከዚህ ፍርድ አምልጦ የሚቆም አይኖርም። ሰዎችንም ይቤዣቸዋል፣ አልያም ለዘላለም በገሃነም ፍርድ ይቀጣቸዋል። ከፍትሐዊነቱም ክብር የተነሣ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ፍትሕ የሚጓደልበት አንዳችም ነገር አይኖርም።)
  • በዓመታት መካከል የቅድስናን ሂደት የታገሠበት የትዕግሥቱ ክብር
  • በሕመም የተሞላውን የመስቀሉን ሥቃይ ለመቀበል እንደ ባሪያ የታዘዘበትየሉዓላዊነቱ ክብር
  • አንድ ቀን በብርታቱ ሲገለጥ፣ ሰዎች ሁሉ የበጉን ፊት ከማየት ይልቅ ድንጋዮችና ተራሮች እንዲወድቁባቸው የሚያስመኛቸው የቁጣው ክብር
  • እንደ እኔ ያለውን ኀጢአተኛ የሚያጸድቀው የጸጋው ክብር
  • ኀጢአተኞች ሳለን የሞተልን የፍቅሩ ክብር

ታዲያ መጋቢ ለሆናችሁ ወንድሞቼ እንዲህ ልበላችሁ፣ ስለዚህ አስደናቂ ስለሆነው የእግዚአብሔር ማንነት በደፈናው ከመናገር ይልቅ፣ በጥልቀትና በስፋት ማስተማር እስካልጀመርን ድረስ፣ እንዲሁም እዚህ ምድር ላይ ካለ ከየትኛውም ነገር ይልቅ እርሱ እጅግ ውብ፣ እጅግም የሚማርክ እንደሆነ በስብከቶቻችን እስካላሳየን ድረስ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ያሉት ትዳሮች ለእግዚአብሔር ክብር መዋል አይችሉም፤ ምክንያቱም እርሱን አያውቁትም። መንፈሳዊ የሚመስሉን የተለያዩ ቃላት ሊጠቀሙ ይችላሉ፤ ነገር ግን እርሱን አያዩትም። ለልጆቻቸውም ስለ እርሱ ማስተማር አይችሉም። ለጎረቤቶቻቸውም ስለ እርሱ መናገር አይችሉም። እንዲሁም ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ስለ እርሱ ማውራት አይችሉም፤ ምክንያቱም ታላላቅ መንፈሳዊ ቃላቶቻቸው ትርጉም የለሽ ናቸው። ይህም ደግሞ የሆነው እኛ በስብከቶቻችን እግዚአብሔርን ስላላከበርነው ነው።

እግዚአብሔር ለማላቅ ያለ መሰጠት

የማገለግልባት ቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮ፣ “እግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ለማላቅ ስላለ መሰጠት በመስበክ፣ ለሕዝቦች ሁሉ ደስታን ማምጣት” የሚል ነው። ይህ ነው ተልእኳችን። ይህንን ጽሑፍ ሳልጨርስ እንኳ ሕይወቴ ቢያልፍ፣ እያደረግሁ የምሞተው ይህንኑ ነው። ከዚህም በኋላ ሌላ 20 ዓመታት ቢጨመሩልኝ፣ በእነዚያ ዓመታት ይህንኑ እንደማደርግ ተስፋ አደርጋለሁ። የተፈጠርኩት እግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ለማላቅ ስላለ መሰጠት በመስበክ፣ ለሕዝቦች ሁሉ ደስታን ለማምጣት ነው። ያለሁትም ለዚሁ ነው። እናንተም የተፈጠራችሁት ለዚሁ ነው። እነዚህን ቃላት መጠቀም አይጠበቅባችሁም፣ ነገር ግን፣ እዚህች ምድር ላይ ያላችሁት ለዚሁ ነው። ታዲያ በትዳር ውስጥ ያሉ ሰዎች ልብ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለማላቅ የተሰጠ እስካልሆነ ድረስ፣ ትዳራቸው ለእግዚአብሔር ክብር የሚኖር አይሆንም።

ጥንዶች የእግዚአብሔርን ክብርና ልዕልና እስካላዩና እስካላወቁ ድረስ፣ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ልብ አይኖራቸውም። ታዲያ መጋቢዎች ሳይታክቱ፣ ያለማቋረጥ፣ በጥልቀት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት፣ እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ በመሆን ካልሰበኩ፣ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ክብርና ልዕልና ሊያውቅ አይችልም። ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር፣ ለእግዚአብሔር ክብር የቆመች ቤተ ክርስቲያን ነጸብራቅ ነው።

ስለዚህ ደግሜ እላለሁ፣ ትዳር የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ክብር፣ ውበት እና እውነት ከፍ አድርጎ እንዲያሳይ ከፈለግን፣ ከትዳር ይልቅ ስለ እግዚአብሔር መስበክና ማስተማር አለብን። ይህንን ስል ታዲያ በተሳሳተ መንገድ እንዳትረዱኝ። ስለ ትዳር አብዝተን እየሰበክን ነው ብዬ አላምንም፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር እጅግ አሳንሰን እየሰበክን ነው። እግዚአብሔር በሕዝባችን ሕይወት ውስጥ ዋና ማዕከል አይደለም። እግዚአብሔር ፀሓያቸው አይደለም።

የሚያበራው ማዕከል

ትልቁ ልጄ፣ በቦስተን ኮሌጅ ይማር በነበረበት ወቅት፣ ደብዳቤዎቹ ላይ እያየኋቸው የነበሩት ነገሮች ስላሳሰቡኝ፣ እኔም አንድ ደብዳቤ ጽፌለት ነበር። ይህንን ታሪክ ለእናንተ መንገሬ የሚያሳስበው አይመስለኝም። በወቅቱ አዲስ ባለ ትዳር፣ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪውን እየሰራ ስለ ነበረ፣ እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ ስለ ነበረው ቦታ እርግጠኛ አልነበርኩም። ስለዚህ አንድ ምስልን ተጠቅሜ፣ እንደ አባቱ ሳይሆን እንደ መጋቢው ሆኜ፣ ረጅም ደብዳቤን ላኩለት። እንዲህ አልኩት፦ “ካርስትን፣ ፀሓይ በዙሪያዋ ላሉ ፕላኔቶች ማዕከል እንደሆነችው ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ክብር ለሕይወትህ እንደዚያ ሆኖ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለው። ታዲያ ከዚህም የተነሳ ፕላኔቶችህ ሁሉ በእግዚአብሔር ክብር ዛቢያ ላይ እየዞሩ እንጂ፣ የትኛውም የሕይወትህ ፕላኔት ማዕከል እንዳልሆነብህ እርግጠኛ ሁን።” ይህንንም አሳብ በደንብ ካብራራሁ በኋላ፣ እንዲህ ብዬ ጸልዬ ላክሁለት፦ “እግዚአብሔር ሆይ፣ እንዲህ ብሎ እንዳይመልስ እርዳው፣ ‘ለ22 ዓመታት ስትሰብክ ሰምቼሃለው፤ ከዚህ በኋላ ይህን መስማት አያስፈልገኝም፤ አመሰግናለው።'”

ከአራት ቀንም በኋላ ደወለልኝ። እየፈራሁ ከባለቤቴ ስልኩን ተቀበልኳት፤ “ደብዳቤህ ደርሶኛል። ከባለቤቴ ሼሊ ጋር አብረን አንብበነዋል። እናመሰግናለን። ይህንን መስማት ያስፈልገን ነበር” አለኝ። ከዚያም ጊዜ በኋላ ነገሮች መልካም ሆኑ፤ በመካከላችንም ግልጽ የሆነ ግንኙነት ተፈጠረ። ያም ደግሞ እጅግ ረድቶናል። ይህንንም ሳስብ እግዚአብሔርን አመሰግናለው። ስለዚህ አሁንም እናንተን ልበላችሁ፤ በቤተ ክርስቲያናችሁ ያሉ ትዳሮች፣ ሁሉን ነገር በዛቢያው እንዲዞር የሚያደርግ ፀሓይ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህንንም የእግዚአብሔር ቦታ፣ ምንም ነገር እንዳይወስደው መጠበቅ አለባቸው። ነገር ግን ለአብዛኞቹ ምዕመኖቻችን ይህ እውነት አለመሆኑ ያስፈራኛል። የተለያዩ መልካም ነገሮች የእግዚአብሔርን ቦታ ነጥቀውባቸዋል። እውነታው ደግሞ ይህ ከሆነ፣ ትዳሮች ለእግዚአብሔር ክብር መዋል አይችሉም።

ስለዚህ እግዚአብሔርን ማወቅና መውደድ፣ እንዲሁም ትዳር አጋራችንን ጨምሮ ከምንም ነገር በላይ ለእግዚአብሔር ክብር ዋጋን መስጠት፣ ትዳርን ለእግዚአብሔር ክብር እንዲውል የሚያደርግ ቁልፍ መረዳት ነው። እንዲህ ብዬ መናገር እወዳለሁ፣ “እግዚአብሔር ከመቼውም ይልቅ በእናንተ የሚከብረው፣ እናንተ ከምንም በላይ በእርሱ ስትረኩ ነው።” ይህ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ያሉን ሺህ በሮች የሚከፍት ቁልፍ ነው ብዬ አምናለው። መዝሙር 63፥3 እንዲህ ይላል፦ “ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና።” ከሕይወት ይበልጣል። ስለዚህ፣ ከሕይወት በላይ በጌታ ምሕረት ልንረካ ይገባል። ይህም ማለት ደግሞ፣ ሞት ራሱ ለደስታችን ስጋት አይደለም ማለት ነው። ታዲያ የእግዚአብሔር ምሕረት ከሕይወት ከበለጠ፣ ከትዳር አጋራችንም ይበልጣል ማለት ነው፤ ምክንያቱም የትኛውንም መልካም ነገር መቅመስ የምንችለው በሕይወት እስካለን ድረስ ብቻ ነው። የጌታ ምሕረት ከሕይወት ከበለጠ፣ ከእግዚአብሔርና ከምሕረቱ ውጪ፣ ከምንም ነገር ይበልጣል ማለት ነው።

የትዕግሥታችን ምንጭ

እግዚአብሔር በክብሩና በክርስቶስ ለእኛ በሆነው ሁሉ መርካት፣ የትዕግሥታችን ምንጭ ነው። ያለዚህ ትዕግሥትም ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ክርስቶስ ሊወዱ፣ ሚስቶችም እንደ ክርስቶስ ሙሽራ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን ባሎቻቸውን ሊከተሉ አይችሉም።

ኤፌሶን 5፥22-25 ግልጽ እንደሚያደርገው ባሎች የመምራት እና የመውደድ ኀላፊነታቸውን ከክርስቶስ ሲማሩ፣ ሚስቶች ደግሞ የመገዛት እና የመውደድ ኀላፊነታቸውን ክርስቶስ ከሞተላት ቤተ ክርስቲያን ይማራሉ። ታዲያ ሁለቱም ኀላፊነቶች እጅግ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው። ጥንዶቹ በዋነኝነት በእግዚአብሔር የማይረኩ ከሆነ፣ ዋጋን በሚያስከፍሉ ከባድ ጊዜያት ላይ መጽናት አይችሉም። ስለዚህ እግዚአብሔርን በትዳር የማክበር ቁልፍ፣ ስንነጋገር የነበረውን ቅደም ተከተል ማስጠበቅ ነው ማለት ነው፤ ይኸውም በቅድሚያና በዋነኝነት በእግዚአብሔር መርካት ነው። ይህ የሚሆን ከሆነ፣ የመምራት እና የመገዛት ኀላፊነቶች አብሮ መሄድ ባቃታቸው ጊዜ እንኳ፣ እንደ ክርስቶስ ለመውደድና እንደ ቤተ ክርስቲያን ለመገዛት የሚያስችላቸውን አቅም ያገኛሉ ማለት ነው። ምንጩ በእግዚአብሔር መርካት ነውና።

በሌላ መንገድ ሳስቀምጠው፣ እግዚአብሔርን በትዳራችን የምናከብርባቸው ሁለት እርከኖች አሉ። አንደኛውን፣ መዋቅራዊ ደረጃ ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ የተነሳሽነት ደረጃ ብለን መጥራት እንችላለን። መዋቅራዊው ደረጃ፣ ሁለቱም የትዳር አጋሮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኀላፊነት የሚወጡበት ነው። ይህም ባል ክርስቶስን በመምሰል ሲመራ፣ ሲወድና ዋጋ ሲከፍል ሲሆን፣ ሚስትም የክርስቶስ መሽራ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን በመከተል ስትገዛ እና የባሏን ምሪት ስትደግፍ፣ ስታከብርና ስትከተል ነው።

ይህ ለባልም ለሚስትም ታላቅ ዋጋን የሚያስከፍል ፍቅር ነው። እናም ይህንን ዋጋ፣ የምኞት መፍለቂያ ከሆነው ከልብ ለመክፈል፣ በቅድሚያ እነዚያ ምኞቶች በዋናነት በእግዚአብሔር ሊረኩ ይገባል። ለዚህም ነው፣ የእርሱ ክብር በእኛ ዘንድ የታወቀ መሆን ያለበት፤ ለዚህም ነው በእርሱ ስንረካ፣ እርሱ የሚከብረው።

ታዲያ፣ እግዚአብሔርን የምናከብርበት ሁለተኛ ደረጃ፣ ማለትም የተነሳሽነት ደረጃ እስካልተሟላ ድረስ፣ እነዚህ ኀላፊነቶች ተጠብቀው መኖር አይችሉም። ይኸውም፣ “እግዚአብሔር ከመቼውም ይልቅ በእኛ የሚከብረው፣ ከምንም በላይ በእርሱ ስንረካ ነው” የሚል ነው። ነገር ግን እነዚህን ኀላፊነቶች በእግዚአብሔር ከመርካት ውጪ ባለ ተነሳሽነት አድርጋችኋቸው ከሆነ፣ እንዲሁም ከግብረ ስጋ ግንኙነት፣ ከትዳር አጋርና ከልጆች ከሚገኝ እርካታ በላይ በእግዚአብሔር በመርካት ካልተጠበቁ፣ ልታደርጓቸው ብትችሉ እንኳ፣ ለራሳችሁ ክብር እንጂ ለእግዚአብሔር ክብር አይውሉም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ፣ ከውበቱ፣ ከክብሩና ከታላቅነቱ አቅምን የምታገኙ ከሆነ፣ እንደ ኢየሱስና እንደ ቤተ ክርስቲያን መውደዳችሁ፣ ኀይላችሁ እርሱ እንደሆነ፣ ደግሞም በእርሱ እንደረካችሁ ማሳያ ይሆናል።

ስለዚህ ከጳውሎስም መማር አለብን። ፊልጵስዩስ 3፥8 እንዲህ ይላል፦

“ከዚህም በላይ ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ።”

በሌላ አነጋገር፣ “ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽራቸው፣ ትዳርን እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ልጆቼን እንደ ጕድለት እቈጥራቸዋለሁ፤ ሚስቴን እንደ ጕድለት እቈጥራታለሁ፤ ባሌን እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ እንዲሁም ግብረ ሥጋ ግንኙነትን እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ” ማለት ነው። በዋነኝነት በኢየሱስ ረክቶ በመቆም፣ እንደ ክርስቶስ እና እንደ ቤተ ክርስቲያን ለመውደድ በየዕለቱ፣ በየሳምንቱና በየወሩ፣ የሚጠይቀውን ራስን የመካድ ኀይል ትቀበላላችሁ።

በጆን ፓይፐር