[እግዚአብሔር] መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል። እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ፤ የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ዘንድ ሊገረም በሚመጣበት በዚያን ቀን ይሆናል። (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥7–10)
ኢየሱስ ቃል እንደገባው ወደዚህች ምድር ሲመለስ፣ በወንጌል ያላመኑት፣ “ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት” እንደሚቀጡ ጳውሎስ ይናገራል። ይህ አማኝ ባልሆኑ ሰዎች ሁሉ ውስጥ ታላቅ ድንጋጤን ሊፈጥር የሚገባ እጅግ አስደንጋጭ ቀጠሮ ነው።
ታዲያ ይህ እውነት እኛ አማኞች ቆም ብለን እንድናስብ እና የጉዳዩ አሳሳቢነት እንዲያስጨንቀን ሊገፋፋን ይገባል። ወንጌልን ላልሰሙ እና ሰምተው ደግሞ ላልተቀበሉ ሰዎች ልባችን በርኅራኄ ሊሞላም ያስፈልጋል።
ታዲያ ግን እዚህ ባለው በመከራችን ደግሞ እንድንጸና ጳውሎስ ሁለት አስደናቂ የማበረታቻ እና የተስፋ ቃላትን እዚሁ ክፍል ውስጥ ይሰጠናል። “[እግዚአብሔር] መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል” በማለት ይጀምራል። በዘመን ፍጻሜ እየከረረ የሚሄድ ስቃይ እየደረሰብን ከሆነ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይለናል፦ ጽኑ! ዕረፍታችሁ በደጅ ነው። መከራችሁ ፍጻሜያችሁ አይደለም። የገዘፉ የሚመስሉ ጠላቶቻችሁም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያዋከቡበትን ቀን በጸጸት የሚረግሙበት ቀን ይመጣል።
ይህን ካለ በኋላ፣ አስደናቂውን የማበረታቻ እና የተስፋ ቃል ይሰጠናል። ጌታ ሲመጣ እፎይታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ የተፈጠርንለትን ታላቅ የህይወት ልምምድ እንቀዳጃለን። ክብሩን እያየን በአድናቆት ፈዘን እንቀራለን። በዚህም ዓለም ሁሉ እኛን እየተመለከተ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ይከብራል።
ቁጥር 10፦ “…በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ዘንድ ሊገረም በሚመጣበት በዚያን ቀን…” ይላል። ለመገረም እና ለመደነቅ ተፈጥረናል። ከተሰቀለው፣ ከሞት ከተነሣውና ከሚመለሰው የክብር ንጉስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ የሚያስደንቅ ምንም እና ማንም የለም። “ታላቁ መገረም” በሆነው በክርስቶስ፣ እንከን እና ኃጢአት በሌለበት ዘለዓለማዊ አድናቆት መገረም ስንጀምር እርሱ የክብሩን ፍጻሜ ያገኛል፤ እኛም የደስታችን ፍጻሜ እንቀዳጃለን።