የከበረው የማርያም አምላክ | ታሕሳስ 6

ማርያምም እንዲህ አለች፦
ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥
መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና።
እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤
ስሙም ቅዱስ ነው።
ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤
ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤
ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤
ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ
ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው
እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።

የሉቃስ ወንጌል 1፥46-55

ማርያም ስለ እግዚአብሔር አንድ ጥርት ያለ ነገር ተመልክታለች። የዓለምን ታሪክ በአስደናቂ መንገድ የሚለውጥ እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነ የሠላሳ ዓመት ታሪክ ሊጀምር እንደሆነ ገብቷታል።

እና በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የት አለ? ማንነታቸው ከማይታወቅ ሁለት ትሑታን ሴቶች ጋር ሥራ ጀምሯል። አንዲት የመውለጃዋ ጊዜ ያለፈባት መካን ሴት፦ ኤልሳቤጥ፣ እና አንዲት ወንድ የማታውቅ ድንግል ሴት፦ ማርያም። ማርያምም በዚህ ትሑታንን በሚወድ የእግዚአብሔር ራዕይ ልቧ በፍቅር ተማርኮ መዝሙር አፈለቀ። መዝሙሩም ታዋቂው “የማርያም መዝሙር” ተባለ።

ማርያም እና ኤልሳቤጥ በሉቃስ ዘገባ ውስጥ ጀግና ሴቶች ሆነው ተስለዋል። ሉቃስ የእነዚህን ሴቶች እምነት ይወደዋል። ሉቃስ በእነዚህ ሴቶች በጣም የሚኮራበት እና ለደብዳቤው ተቀባይ ለቴዎፍሎስም ሊነግር የፈለገው አንድ ነገር፣ እንዴት ባለ ጭምትነት እና ደስታ በሞላበት ትሕትና ለከበረው አምላካቸው ለእግዚአብሔር እንደተገዙ ነው።

ሉቃስ ወንጌል 1፥43 ላይ ኤልሳቤጥ እንዲህ ትላለች፤ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” ማርያምም ደግሞ ወረድ ብሎ ቁጥር 48 ላይ “…የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ትላለች።

ነፍሳቸው በእውነተኛው መንገድ አምላካቸውን ሊያከብር የሚችሉ ሰዎች እንደ ኤልሳቤጥ እና ማርያም ዐይነቶቹ ናቸው። ዝቅ ያለውን ቦታቸውን የሚቀበሉ እና የከበረው አምላክ መዋረድ የሚደንቃቸው ሰዎች በርግጥ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።