ለሚስዮናዊው የሚሆን መድኀኒት | ጥቅምት 19

በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” (ማርቆስ 10፥27)

የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጸጋ ለክርስቲያን ሄዶኒስቶች የሕይወት ምንጭ የሆነ ውሃ ነው። ከምንም በላይ በፀጋው ውስጥ መኖር እና ለሌሎች ማካፈል ለክርስቲያን ሄዶኒስቶች አስደሳች ነው።

ክርስቲያን ሄዶኒስት የሆኑ ሚስዮናውያን፣ “ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው” የሚለውን ሕይወት ይወዱታል (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)። የልፋታቸው ፍሬ በእግዚአብሔር የሚወሰን በመሆኑ፣ በዚህ እውነት ላይ ያርፋሉ (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥7ሮሜ 11፥36)።

አምላካቸው “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” ሲል ደስታ ነው የሚሰማቸው (ዮሐንስ 15፥5)። እግዚአብሔር አዲስ ነፍሳትን የማዳን ከባድ ሸክም ከእነርሱ ትከሻ ላይ አንስቶ ራሱ ትከሻ ላይ እንዳኖረው ሲያስቡ እንደ ጠቦት በደስታ ይቦርቃሉ። ያለ ማመንታት “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም” ይላሉ (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥5)።

ስራቸውን አጠናቅቀው ወደቤታቸው ሲመለሱ፣ ለአብያተ ክርስቲያናት “በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም” እያሉ በደስታ ይናገራሉ (ሮሜ 15፥18)።

“በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል!” – ቃላቱ በአንድ በኩል ተስፋ ሰጭ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ትሑት እንድንሆን ያደርጉናል። ለጭንቀት እና ለኩራት የሚሆኑ ፍቱን መድኀኒት ናቸው – ለሚስዮናዊው ምርጡ መድኀኒት።