ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3፥22–23)
የእግዚአብሔር ምሕረት በየማለዳው አዲስ ነው፤ ምክንያቱም ደግሞ እያንዳንዱ ቀን ለዚያ ቀን ብቻ የሚበቃ ምሕረት ስላለው ነው። የየቀኑ ችግሮች በእግዚአብሔር የተወሰኑ ናቸው። የየቀኑ ምሕረቶችም እንደዛው። በልጆቹ ሕይወት ውስጥ፣ እያንዳንዳቸው በትክክል በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ኢየሱስም እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና” (ማቴዎስ 6፥34)። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ ችግር አለው። እያንዳንዱ ቀንም የራሱ ምሕረት አለው። በየጠዋቱ አዲስ ናቸው።
እኛ ግን የነገን ሸክም በዛሬ ሀብት መሸከም እንዳለብን ስናስብ ብዙ ጊዜ ተስፋ እንቆርጣለን። እግዚአብሔር ግን ያን ማድረግ እንደማይጠበቅብን እንድናውቅ ይፈልጋል። የዛሬ ምሕረቶች ለዛሬ ችግሮች ናቸው። የነገ ምሕረቶችና ጸጋዎች ደግሞ ለነገ ችግሮች ናቸው።
አንዳንድ ጊዜ በአስፈሪ ፈተና መካከል ስናልፍ፣ የምንቆምበትን ምህረት እናገኝ ይሆን ወይ ብለን እንጨነቃለን። አዎ፣ እናገኛለን። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥14)። ስድቡ ሲመጣ፣ የክብር መንፈስ ይመጣል። እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወገር የሆነው ይህ ነው። ታዲያ ይህ ለእናንተም ይሆናል። መንፈሱና ክብሩ በሚያስፈልጉበት ሰዓት ይመጣሉ።
የምድረበዳው መና ለአንድ ቀን ብቻ እንዲሆን የተሰጠ ነበር። ማከማቸት የሚባል ነገር የለም። በእግዚአብሔር ምሕረትም ላይ መደገፍ ያለብን እንደዚያ ነው። የነገን ሸክም ለመሸከም የሚያስችል ጥንካሬን ዛሬ አትቀበሉም። ለዛሬ ችግሮች የሚሆኑ የዛሬ ምሕረቶች ተሰጥተዋችኋል።
ነገ ምህረቶቹ አዲስ ይሆናሉ። “ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥9)።