ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
የማቴዎስ ወንጌል 2፥1-2
ከሉቃስ በተለየ መልኩ ማቴዎስ ስለ እረኞቹ የበረት ጉብኝት አይነግረንም። ይልቁኑም አትኩሮቱን ከምሥራቅ በኩል ወደ መጡት አይሁዳዊ ያልሆኑ አሕዛብ (የውጭ ዜጎች) ላይ ያደርጋል።
ማቴዎስ በወንጌሉ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ፣ ኢየሱስ ዓለም ዐቀፍ መሲሕ መሆኑን እና ሊያድን የመጣው አይሁድን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ሁሉ እንደሆነም ያስረዳናል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አምላኪዎች የሆኑት የንጉሥ አስማተኞች ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች ወይም ጠቢባን ከእስራኤል የመጡ ሳይሆኑ ከምሥራቅ አካባቢ፣ ምናልባትም ከባቢሎን ግዛት የመጡ አሕዛብ ናቸው። አሕዛብ በአይሁድ የብሉይ ኪዳን የመንፃት ሕግጋት መሠረት የረከሱ ሰዎች ነበሩ።
በማቴዎስ ወንጌል መጨረሻ የኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት እኚህ ነበሩ፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፥18-19)።
ይህ እውነት አሕዛብ ለሆንን ለእኛ፣ በመሲሑ መደሰት የምንችልበትን በር ከመክፈቱ ባሻገር፣ ነገሥታት እና ሕዝቦች ሁሉ ወደ እርሱ የሚመጡለት የዓለም ገዢ እንደሚሆን በተደጋጋሚ የተተነበየለት መሲሑ መሆኑን ማረጋገጫ ሆኗል። ለምሳሌ፤ ኢሳይያስ 60፥3፦ “ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ጸዳል ይመጣሉ።”
በዚህም ማቴዎስ ኢየሱስ እውነተኛው መሲሕ ለመሆኑ ማስረጃ የጨመረ ሲሆን፣ ከዚህም ባለፈ ኢየሱስ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የሚሆን እውነተኛ መሲሕ፣ ንጉሥ፣ እና የተስፋ ቃሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ያሳየናል።