“እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራቸው” ይላል እግዚአብሔር (ኤርምያስ 1፥8)።
ከሰዎች ዘንድ ሊመጣ የሚችል ተቃውሞን እና ተቃርኖን መፍራት የአገልግሎት ትልቁ እንቅፋት ነው። ይህ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ይበልጥ የሚታይ ነገር ነው።
ሰዎች ምን ይሉናል ብለን ብዙ እናስባለን። “በምናገረው ወይም በማደርገው ነገር ሰዎች ቢቀየሙኝስ፣ ባይስማሙስ፣ ቢቆጡስ?” ብለን እንጨነቃለን። “ብሳሳትስ? ወቀሳቸውን አልችለውም” ብለን እንታወካለን።
በርግጥም ሰውን መፍራት ታማኝ ለሆነ አገልግሎት ትልቅ እንቅፋት ነው።
እግዚአብሔር ግን፣ “አትፍሩ እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤ አድናችኋለሁ” ይላል። የእግዚአብሔር መገኘት እና በእርሱ ዘንድ የሚገኝ ተቀባይነት የዓለም ሕዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ከሚሰጠው እውቅና እና ሽልማት ይልቃል። ከጭንቀቶቻችን ሁሉ ነፃ ሊያወጣን፣ በመጨረሻም አሸናፊዎች ሊያደርገን ቃል ገብቶልናል። ከአሸናፊዎችም ሁሉ በላይ አደርጋችኋለሁ ብሏል።
እናም ይህ ሁሉ ዛሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ላለን ለእኛ ቃል ተገብቶልናል፦
- “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ ‘ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን” (ዕብራውያን 13፥5-6)።
- “ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?” (ሮሜ 8፥31)
እናም እግዚአብሔር ለወጣቱ ኤርምያስ እንደተናገረው ዛሬም እንዲያገለግሉት ለጠራቸው ወጣቶች እና ለሁላችንም እንዲህ ይላል፦ ‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’፣ ወይም ‘በጣም አርጅቻለሁ’፣ ወይም ‘በጣም የሆነ ነገር ነኝ’ አትበሉ (ኤርምያስ 1፥7)። ለምን?
- ሕይወታችሁ ጽኑ በሆኑ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማዎች ላይ የተገነባ ነው። ለታላቅ ሥራ ተጠርታችኋል፣ ተለይታችኋል፣ ተሰርታችኋል፣ ተመርጣችኋል።
- ከንግግራችሁ እና ከአገልግሎታችሁ ጀርባ ያለው የእግዚአብሔር ሥልጣን እንጂ የራሳችሁ አይደለም።
- ደግሞም ራሱ እግዚአብሔር ከፈተናዎቻችሁ እና ከመከራዎቻችሁ ሁሉ ሊያድናችሁ አብሯችሁ አለ።