ተስፋ መቁረጥን ለመዋጋት የሚያግዙ ምሳሌዎች | ሐምሌ 20

ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው።” (መዝሙር 73፥26)

ይህንን ጥቅስ ጠጋ ብለን ስንመለከት እና ቃል በቃል ግሱን ስናይ “ሊደክሙ ይችላሉ” ሳይሆን የሚለው፣ በቀላሉ “ይደክማሉ” ነው። ይህ በእግዚአብሔር የተወደደው ዘማሪ አሳፍ፣ “ሥጋዬና ልቤ ደክመዋል፤ ተስፋ ቆርጫለሁ! መንፈሴ ወርዷል!” ይላል። ነገር ግን ወዲያው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ላይ ጦርነት በመክፈት፣ “እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታትና የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው” በማለት ያውጃል።

መዝሙረኛው ለተስፋ መቁረጥ እጁን አይሰጥም። አለማመንን በመልሶ ማጥቃት ይዋጋዋል።

በመሠረቱ እያለ ያለው እንዲህ ነው፦ “ውስጤ በጣም ደክሟል፣ አቅመ ቢስ እና መቋቋም የማልችል እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሰውነቴ ደቋል፤ ልቤም ሊሞት ተቃርቧል። ነገር ግን የዚህ ተስፋ መቁረጥ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ እጅ አልሰጥም። እኔ እራሴን ሳይሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ። እርሱ ብርታቴና ዕድል ፈንታዬ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱሳችን በተጨነቁና መንፈሳቸው በተጎሳቆለ ቅዱሳን ታሪክ የተሞላ ነው። መዝሙር 19፥7 “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል” ይላል። የቅዱሳን ነፍስ አንዳንድ ጊዜ መቀስቀስ እንደሚያስፈልገው ያሳየናል። መቀስቀስና መለምለም ካለበት ደግሞ በሆነ መልኩ ሞቶ ነበር ማለት ነው። ስሜቱም እንደዛ ነው።

ዳዊትም በመዝሙር 23፥2-3 ላይ በተመሳሳይ መልኩ፣ “በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል” ይላል። “ለእግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነለት” ነፍስ፣ መታደስና መመለስ አስፈልጎታል (1ኛ ሳሙኤል 13፥​14)። በጥም ወድቆ ለመሞት ጫፍ ላይ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ነፍሱን ወደ ውሃ መራለትና እንደገና ሕይወትን ሰጠው።

እግዚአብሔር እነዚህን ምስክርነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠው አለማመንን እና ተስፋ መቁረጥን እንድንዋጋባቸው ነው። እኛም በእግዚአብሔር ተስፋዎች በመታመን፣ “እግዚአብሔር የልቤ ብርታትና የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው” እያልን እንታገላለን። ያንንም ለራሳችን ዘወትር እንሰብካለን። ሰይጣንን እንዋጋበታለን። በዚያም እንታመናለን። በእምነትም እንኖራለን።