ዋላ የምንጭ ውሃ እንደምትናፍቅ፣ አምላክ ሆይ፤ ነፍሴም እንዲሁ አንተን ትናፍቃለች። ነፍሴ አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማች፤ መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው? (መዝሙር 42፥1-2)
ይህን መዝሙር ለእኛ አስደናቂ እና እጅግ ወሳኝ የሚያደርገው፣ ጥማቱ በዋናነት ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት አለመሆኑ ነው። የእርሱ ጥማት በዋነኛነት ከጠላቶቹ ማምለጥ ወይም የእነርሱን መጥፋት መፈለግ አይደለም።
እረፍትን ለማግኘት መፈለግ እና ስለዚያም መጸለይ ስሕተት አይደለም። ጠላቶች እንዲሸነፉ መጸለይ አንዳንድ ጊዜ ትክክል ነው። ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጠው እግዚአብሔር ራሱ ነው።
በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔርን ስናስበውና ስሜቱን ስንጋራ ውጤቱ የሚሆነው ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን እንወደዋለን ደግሞም እግዚአብሔርን ለማየት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን፣ እርሱን በማድነቅ እና እርሱን ከፍ በማድረግ ልንረካ እንፈልጋለን።
የቁጥር 2 ተቀራራቢ ትርጓሜው “መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው?” የሚለው ነው። ለዚያ ጥያቄ የመጨረሻው መልስ የተሰጠው በዮሐንስ 14፥9 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4 ላይ ነው። “እኔን ያየ አብን አይቶአል።” ጳውሎስ ደግሞ ወደ ክርስቶስ በንስሓ በተመለስን ጊዜ “የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን” እናያለን ይላል።
የክርስቶስን ፊት ስናይ የእግዚአብሔርን ፊት እናያለን። ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4 እና 6 ላይ ወንጌሉ የሆነውን የክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤ ታሪክ ስንሰማ፣ የክርስቶስን ፊት ክብር እናያለን በማለት ይናገራል። ደግሞም ይህንን “የእግዚአብሔር አምሳል የሆነው የክርስቶስ የክብሩን ወንጌል ብርሃን” በማለት ይገልጸዋል። ቁጥር 6 ላይ ደግሞ፣ “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን” እንደገለጠ ይነግረናል።
የእግዚአብሔርን ፊት ለማየት ያላችሁን ረሀብ እና ጥማት ራሱ እግዚአብሔር ይጨምር። የእግዚአብሔር አምሳል በሆነው በክርስቶስ ክብር ወንጌል ዛሬም ቢሆን መሻታችሁን ይሙላ።