“አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል።” መዝሙር 115፥3
ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር በሚሠራበት ጊዜ ሁሉ እርሱን በሚያስደስት መንገድ እንደሚሠራ ያስተምራል።
እግዚአብሔር የማይፈልገውን እና የሚጠላውን ነገር ለማድረግ ቅርቃር ውስጥ ፈጽሞ አይገባም፤ ደግሞም አይገደድም።
ደስ የሚያሰኘውን ያደርጋል። ስለዚህም በአንድ መልኩ በሚያደርገው ሁሉ እርካታ አለው።
ይህ በእግዚአብሔር ፊት እንድንሰግድና ሉዓላዊ ነፃነቱን እንድናወድስ ሊመራን ይገባል፤ ይህም እርሱ “እንደ በጎ ፈቃዱ” የራሱን ደስታ በመከተል ሁል ጊዜ በነፃነት ይሠራል ማለት ነው።
እግዚአብሔር በፍጹም የሁኔታዎች ሰለባና ተጠቂ አይሆንም። እርሱ ደስ የማያሰኘውን ነገር ወደሚያደርግበት ሁኔታ በጭራሽ ተገድዶ አይገባም። አይዘበትበትም። እርሱ በጭራሽ በሁኔታዎች አይጠመድም፣ መውጫ በሌለው ቅርቃር ውስጥ አይገባም፤ ደግሞም በምንም መልኩ ግዳጅ ውስጥ አይገባም።
በታሪክ ውስጥ በአንድ ወቅት፣ በሆነ መልኩ እግዚአብሔር ሊያደርገው በጣም ከባድ የሆነውን “ለገዛ ልጁ አለመራራትን” (ሮሜ 8፥32) ባደረገበት ወቅት እንኳ እርሱ የወደደውን አድርጓል። ጳውሎስ የኢየሱስን ራሱን አሳልፎ መስጠት፣ “መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት … ለእግዚአብሔር” (ኤፌሶን 5፥2) ይለዋል። ታላቁ ኀጢአት፣ ታላቁ ሞት እና የእግዚአብሔር ከባዱ ተግባር በሙሉ አብን ደስ የሚያሰኝ ነበር።
ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ኢየሱስ ራሱ ለያዝዛቸው የሚችሉ መላእክት ነበሩት፤ ነገር ግን “ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤” ብሏል(ዮሐንስ 10፥18)፤ እንዲሁም ዕብራውያን 12፥2 ላይ “በፊቱ ስላለው ደስታ” ይላል። በታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ወጥመድ ውስጥ የገባ በመሰለበት ጊዜ እንኳ እርሱ የወደደውን እያደረገ ነበር። ይኸውም እንደ እኔና አንተ ያሉትን ኀጢአተኞችን በማጽደቅ አባቱን ማክበር ነው።
ስለዚህ በፍርሃትና በመደነቅ በፊቱ እንቁም። ስለ እግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ያለን ምሥጋና ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ሞት ያገኘነው መዳናችን በዚህ እውነት ላይ ያረፈ በመሆኑ በመንቀጥቅጥ በፊቱ እንቅረብ፤ “አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል።”