በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።
የሉቃስ ወንጌል 2፥6-7
እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ አንቀሳቅሶ ማርያም እና ዮሴፍን ወደ ቤተ ልሔም ለማስመጣት ዓለም አቀፍ የሆነ ቆጠራ ካሰናዳ የሚያርፉበት ማደሪያ ሊያዘጃግላቸው አይችልም ነበር?
አዎ፤ በርግጥ ያለምንም ጥርጥር ሊያዘጋጅላቸው ይችል ነበር። ኢየሱስም ሀብታም ከሆኑ ቤተሰቦች ሊወለድ ይችል ነበር። በበረሃ ድንጋዩን ወደ ዳቦ መለወጥ ይችል ነበር። በጌትሰማኔ ዐሥር ሺህ መላእክትን ማዘዝ ይችል ነበር። ከመስቀል ወርዶ ራሱን ማዳን ይችል ነበር። ጥያቄው እግዚአብሔር ምን ማድረግ ይችል ነበር ሳይሆን፣ ምን ማድረግ ፈቀደ ነው።
ምንም እንኳን ክርስቶስ ባለጠጋ ቢሆንም፣ ለእናንተ ሲል መደኽየቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። በቤተ ልሔም ከተማ ባሉ ማደሪያዎች ሁሉ “አልጋ የለም” የሚሉት ምልክቶች ሁሉ የተሰቀሉት ስለእናንተ ነው። “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ” (2ኛ ቆሮንጦስ 8፥9)።
እግዚአብሔር በሁሉም ነገር ላይ ይገዛል። ስለ ልጆቹ ሲል የሆቴል ማደሪያዎችን እና የሚከራዩ ክፍሎችን ሁሉ ሳይቀር ያስተዳድራል። የቀራንዮ መንገድ የሚጀምረው በቤተ ልሔም ከተማ “አልጋ የለም” በሚል ምልክት ሲሆን ማብቂያው ደግሞ በኢየሩሳሌም ከተማ በመስቀል ላይ ሲሰደብ እና ሲተፋበት ነው።
ኢየሱስ የተናገረውን ደግሞ ልንዘነጋ አይገባም። “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ” (ሉቃስ 9፥23)።
በቀራንዮ መንገድ ላይ አብረነው እየተጓዝን እንዲህ ሲል እንሰማዋለን፤ “ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ” (ዮሐንስ 15፥20)።
“ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” ብሎ ለሚጣራው እንዲህ ይመልስለታል፦ “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” (ሉቃስ 9፥57-58)።
አዎ፤ በርግጥ እግዚአብሔር ለኢየሱስ መወለጃ የሚሆን ክፍል ማዘጋጀት ይችል ነበር። ያ ግን ከቀራንዮ መንገድ ወጥቶ ወደሌላ አቅጣጫ መታጠፍ ይሆን ነበር።