“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።” (ማቴዎስ 6፥19–20)
በትላልቅ ባንክ ቤቶች እና የፋይናንስ ተቋማት በጩኽት መጠየቅ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ይህ ነው፦ እናንተ ዓለማውያን ሰዎች! በቃ ይህ ነው የሚያረካችሁ!?
ብል በሚበላው፣ በዋጋ ንረት በሚያሽቆለቁልና በሞት ዝገት ሊበሰብስ በሚችል ጥቂት ሃብት አትርኩ። ይልቁንስ መለኮታዊ ዋስትና በተሰጣቸው ሰማያዊ ተስፋዎች ላይ አተኩሩ።
ሕይወታችሁን እንደ ገንዘብ አስቡት። ሕይወትን ለቁሳዊ ምቾት፣ ደህንነትና ደስታ አሳልፎ መስጠት፣ ገንዘብን ወደ አይጥ ጉድጓድ እንደ መጣል ነው። ነገር ግን የሕይወትን ገንዘብ በፍቅር ሥራ ላይ ማዋል እጅግ የላቀ እና ለዘለዓለም ዘላቂ የሆነን የደስታ ትርፍ ያስገኛል፦
“ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ንብረት በሰማይ አከማቹ” (ሉቃስ 12፥33)። ይህ መልእክት እጅግ መልካም ዜና ነው፦ ኑ ወደ ክርስቶስ! በፊቱ የዘላለም ደስታና ተድላ አለ። ኑ እውነተኛ እርካታን ለማግኘት እንትጋ። ጌታ ተናግሯልና፦ አሁን ቢሆን ለዘላለም፣ በቅንጦት ከመኖር ይልቅ በፍቅር መኖር ይበልጥ የተባረከ ነው!