ለጥቂት ጊዜ ብቻ | ጥር 9

በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። (1ኛ ጴጥሮስ 5፥10)

አንዳንዴ በመከራ እና በተለመዱ የዕለት ተዕለት ጭንቀቶች መካከል፣ “ጌታ ሆይ እስከ መቼ? ዛሬ ከሚሰማኝ ሕመም አሻግሬ ማየት አልቻልኩም። ነገም ደግሞ ሌላ መከራ ይዞብኝ ይመጣ ይሆን? ነገም ላይ አንተ ከጎኔ ትሆን ይሆን?” ብለን እንጮኽ ይሆናል።

ይህ ጥያቄ እጅግ አሳሳቢ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ፣ “እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል” ብሏል (ማርቆስ 13፥13)። “ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት” መካከል መሆንን ስናስብ እንንቀጠቀጣለን (ዕብራውያን 10፥39)። የያዝነው ቀልድ አይደለም። መከራ፣ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ ለሚኖረን እምነት አስጊ የሆነ እንቅፋት ነው።

ስለዚህ ጴጥሮስ በመከራ ውስጥ ላሉ እና ለዛሉ ክርስቲያኖች፣ “ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል” ብሎ ቃል ሲሰጣቸው መስማት የሚያስደስት ነገር ነው (1ኛ ጴጥሮስ 5፥10)።

መቋቋም ከምንችለው በላይ እንደማይዘገይ፣ የምናለቅስባቸውን ጉድለቶች እንደሚያስወግድ እና ለረጅም ጊዜ የተናወጠውን ነገር ለዘላለም እንደሚያጸና የተሰጠን ማረጋገጫ የመጣው፣ “የጸጋ ሁሉ” አምላክ ከሆነው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው።

እግዚአብሔር የአንዳንድ ጸጋ ብቻ አምላክ አይደለም። እርሱ “የጸጋ ሁሉ አምላክ” ነው፤ እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስፈልገንን፣ ማለቂያ የሌለውን የወደ ፊቱን የጸጋ ክምችት ጨምሮ አትረፍርፎ ይሰጠናል።

ባለፈው የጸጋ ትውስታ የጠነከረ፣ በመጪው ጸጋ ላይ ያለ እምነት፣ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብና አስቸጋሪ መንገድ ላይ ለመጽናት ቁልፍ ነው።