በእርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን። (ሮሜ 5፥2)
ከሁሉ የላቀው ተስፋችን የእግዚአብሔርን ክብር ማየት ነው። “የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን” ይላል (ሮሜ 5፥2)። እግዚአብሔር “ያለ ነቀፋና በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ” ይቻለዋል (ይሁዳ 24)።
እርሱ “አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ” ያደርጋል (ሮሜ 9፥23)። ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ጠርቶናል (1 ተሰሎንቄ 2፥12)። የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ መጠባበቅ የተባረከው ተስፋችን ነው (ቲቶ 2፥13)።
ኢየሱስ በማንነቱ እና በስራው ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ክብር ሥጋዊ እና የመጨረሻ መገለጥ ነው። “እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ” ነው (ዕብራውያን 1፥3)። ኢየሱስ በዮሐንስ 17፥24 ላይ እንዲህ ብሎ ጸልዯል፦ “አባት ሆይ፤ … እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ … ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ።”
“እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ፣ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፣ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ” ይላል (1ኛ ጴጥሮስ 5፥1)። “ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው” (ሮሜ 8፥21)።
“እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን” (1 ቆሮንቶስ 2፥7)። “ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል” (2 ቆሮንቶስ 4፥17)። “ያጸደቃቸውን አከበራቸው” (ሮሜ 8፥30)።
በክርስቶስ ወንጌል አማካኝነት የእግዚአብሔርን ክብር ማየት ደግሞም የዚያ ተካፋይ መሆን፣ የመጨረሻው ተስፋችን ነው። ይህን የመሰለ ውድ የሆነ ተስፋ፣ አሁን ላይ በምናስበልጣቸው፣ በምንመርጣቸው፣ እና በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ እጅግ ወሳኝ የሆነ ሚና ይኖረዋል።
የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ እደጉ። ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለ ክርስቶስ ክብር በጥልቀት አጥኑ። የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠውን የዚህን ዓለም ክብር፣ ደግሞም የክርስቶስን ክብር የሚገልጠውን የወንጌሉን ክብር ከልባችሁ መርምሩ።
የእግዚአብሔርን ክብር ከሁሉ ነገር በላይ ውድ ሀብታችሁ አድርጉት። በሁሉም ነገራችሁ ላይ አንግሡት።
ነፍሳችሁን አጥኑ። የሚያማልላችሁን ክብር እወቁት፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ያልሆኑ ክብሮችን ለምን አስበልጣችሁ እንደምትፈጉ ድረሱበት። በ1ኛ ሳሙኤል 5፥4 ላይ የአሕዛብ ጣዖት የሆነው ዳጎን እንደወደቀ ሁሉ፣ የዓለምን ክብር መጣል እንዴት እንደሚቻል ለማወቅ ነፍሳችሁን አጥኑ። ከእግዚአብሔር ክብር የሚያሰናክሏችሁ ክብሮች ሁሉ ተሰባብረው በዓለም ቤተ መቅደስ መሬት ላይ ይውደቁ። ከዚህ ዓለም ሁሉ በላይ የእግዚአብሔርን ክብር ውድ ሀብታችሁ አድርጉት።