“‘መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ። ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’” (ኤርምያስ 32፥40-41)
እግዚአብሔር ከእኛ ምስጋናን መፈለጉ እና እኛ ደግሞ ደስታና እርካታን በእርሱ ውስጥ መፈለጋችን ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው። እግዚአብሔር ክብሩን መሻቱ፣ እኛ ደግሞ ፍጹም እርካታን መፈለጋችን ከግብ የሚደርሱት በዚህ አንድ እውነት በኩል ነው፦ በእግዚአብሔር ደስ በመሰኘታችን ውስጥ። ይህም አምልኮን ያዘለ ነው።
እግዚአብሔር አምልኮን የሚያየው በሕዝቦቹ ልብ ውስጥ የታላቅነቱ ጥዑም ዜማ የሚያስተጋባበት መንገድ አድርጎ ነው።
ለእኛ ደግሞ ምስጋናችን ከእግዚአብሔር ጋር ከምናደርገው ሕብረት የሚመነጭ የታላቅ ደስታችን መገለጫ ነው።
ታዲያ የሚያስደንቀው ነገር እግዚአብሔር ክብሩን የሚፈልግበት መለኮታዊ ኅይል ራሱ፣ ለእኛ በእርሱ ደስታችንን ለምንፈልግ ሁሉ መልካም እንዲያደርግልን የሚገፋፋው መሆኑ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መልካም ዜና ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በእርሱ ተስፋ ላደረጉት ሰዎች፣ የልብ እርካታቸውን ለመሙላት ችላ አይልም። እንዲያውም ለእኛ ፍጹም እርካታ በሚሰጠን ነገር፣ የእርሱም ነፍስ ሐሴት ታደርጋለች። እነዚህ አስገራሚ ቃላት ናቸው፦ “ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ” (ኤርምያስ 32፥41)።
እግዚአብሔር በሙሉ ልቡ እና መገኘቱ የእኛን ዘላለማዊ ደስታ ይጋራናል፤ ምክንያቱም የዚህ ደስታ መፈፀም ከራሱ ክብር ጋር የተቆራኘ ነውና።