ጥቅማችን ክብሩ ነው | መስከረም 22

አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። (ማቴዎስ 6፥6)

የ”ክርስቲያን ሄዶኒዝም” (Christian Hedonism) አስተምህሮን ለመቃወም ብዙ ጊዜ የሚነሣው የተቃውሞ ነጥብ፣ የሰውን ፍላጎት ከእግዚአብሔር ክብር ማስቀደሙ ነው፤ ማለትም ደስታዬን ከእግዚአብሔር ክብር በላይ ያደርገዋል የሚል ተቃውሞ ነው። ነገር ግን “ክርስቲያን ሄዶኒዝም” ደስታዬን ከእግዚአብሔር ክብር በላይ አያደርግም።

ክርስቲያን ሄዶኒስት” (Christian Hedonists) የሆንን ሁላችን፣ በሙሉ ኃይላችን ፍላጎታችንን እና ደስታችንን ለማግኘት እንጥራለን። ጆናታን ኤድዋርድስ በወጣትነቱ የነበረውን ቁርጠኝነት፣ እኛም እንጋራዋለን፦ “ውሳኔ፦ በሙሉ ኅይል እና ጉልበት፣ የምችለውን ያህል ደስታ ከዚያኛው ዓለም አገኝ ዘንድ በብዙ መሰጠት እጥራለሁ።”

ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ (እና ከኤድዋርድስ) እግዚአብሔር ለእኛ ምሕረትን በማፍሰስ፣ የክብሩን ሙላት ማጉላት እንደሚፈልግ ተምረናል፤ እግዚአብሔር እጅግ የሚያስፈልገን ኃጢአተኞች ነን።

ስለዚህ ፍላጎታችንንና ደስታችንን ማሳደድ፣ ሕይወታችንን የሚያስከፍል ቢሆን እንኳ ከእግዚአብሔር ፍላጎት፣ ከእግዚአብሔር ደስታ እና ከእግዚአብሔር ክብር በላይ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት እጅግ ውድ እውነቶች አንዱ፣ የእግዚአብሔር ትልቁ ፍላጎት ኃጢአተኞችን በእርሱ ደስ በማሰኘት የጸጋውን ባለጠግነት ማጉላት ነው።

ራሳችንን እንደ ሕፃናት ስናዋርድና ብቁ እንደሆንን ሳናስመስል፣ ይልቅ በደስታ ወደ አባታችን እቅፍ ስንሮጥ፣ የጸጋው ክብር ደምቆ ይታያል፤ የነፍሳችንም ናፍቆት ይረካል። ፍላጎታችንና ክብሩ አንድ ይሆናል።

ኢየሱስ በማቴዎስ 6፥6 ላይ፣ “በስውር የተደረገውን የሚያይ አባታችሁ ዋጋችሁን ይከፍላችኋል” በማለት የተስፋን ቃል ሲሰጠን፣ ይህ እንድንሻ የሚፈልገው ሽልማት ነው። ልንጨብጠው በማንችለው ደስታ አያታልለንም! ነገር ግን ይህ ሽልማት፣ ማለትም ይህ ደስታ ከሰው ምስጋና በመራቅ እና እግዚአብሔርን ለመፈለግ ወደ ክፍላችን በመግባት የሚትረፈረፍ ነው።

ስለዚህ “ክርስቲያን ሄዶኒስቶች” (Christian Hedonists)፣ ደስታቸውን ከእግዚአብሔር ክብር በላይ አያስቀምጡም፤ ደስታቸውን በእግዚአብሔር ክብር ላይ ያደርጋሉ። ከምንም ነገር በላይ በእግዚአብሔር ስንረካ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ እግዚአብሔር በእኛ ይከብራል።