“የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።” (ማርቆስ 10፥45)
ኢየሱስ፣ ሕዝቡን ማገልገሉ በዚህ ምድር ሲኖር ብቻ ሆኖ አያበቃም። ዳግም ሲመጣም አገልጋያችን ይሆናል። “ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል” (ሉቃስ 12፥37)። ኢየሱስ ይህንን ያለው በሚመለስበት ጊዜ የሚያደርገውን ለማሳየት ነው።
ወደፊት ብቻም አይደለም፣ እርሱ አሁንም አገልጋያችን ነው። “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሎአል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” የምንልበት አቅም አለን (ዕብራውያን 13፥5-6)።
ታዲያ ግን፣ “ኢየሱስ የገዛ ሕዝቡ አገልጋይ ነበር፣ አሁንም ነው፣ ወደፊትም ይሆናል” ማለት፣ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስን ክብር የሚያቃልል ነገር ይሆን? “አገልጋይ” ስንል የምንልበት መንገድ ይወስነዋል። ትእዛዝን የሚቀበልና የበታች እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ እኛ የእርሱ ጌቶች እንደሆንን ካሰብን አዎን ያሳንሰዋል። እንዲያውም ያዋርደዋል። ነገር ግን፣ ደካሞች በመሆናችን የእርሱን አገልግሎት ዘወትር እንፈልጋለን እያልን ከሆነ ግን ክብሩን ማቃለል አይደለም።
ከሁሉ በላይ እጅግ የሚያስፈልገንን አገልግሎት ሊሰጠን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው ማለት እርሱን ማቃለል አይሆንም።
አገልጋያችን ከማያልቀው የፍቅር ምንጩ በረዳን ልክ፣ እኛም በእርሱ አገልግሎት ላይ እየተደገፍን እንሄዳለን፣ የስጦታዎቹንም አስደነቂነት እናጣጥመዋለን። በልበ ሙሉነትም “ኢየሱስ ሕያው የሆነው ሊያገለግል ነው!” ማለት እንችላለን። ይህም አያሳንሰውም።
ሕያው የሆነው ለማዳን ነው። ሕያው የሆነው ለመስጠት ነው። እንዲህ በማድረጉም እጅግ ደስ ይሰኛል።
እርሱ የእናንተ ጭንቀት አይከብደውም፣ ትከሻው አይጎብጥም። ሸክም ከመስጠት ይልቅ ሸክምን ማቃለል ማንነቱ ነው። “በተስፋ ለሚጠባበቁት” መልካምን ሁሉ ማድረግ ይወዳል (ኢሳይያስ 64፥4)። “በምሕረቱ በሚታመኑት ይደሰታል (መዝሙር 147፥11)። በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ (2ኛ ዜና 16፥9)።
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሁሉን ቻይ በሆነ አገልግሎቱ፣ የሚያምኑትን ሁሉ በማገልገል እጅግ ደስተኛ ነው።