እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለ መገረዝ ሙታን ሳላችሁ፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። የአለቆችንና የባለ ሥልጣናትንም ማዕረግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ። (ቆላስይስ 2፥13-15)
ለአንድ አማኝ ከክርስቶስ ጋር ያለው አንድነት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣበት ምክንያት ክርስቶስ በቀራንዮ በዲያብሎስ ላይ ወሳኝ ድልን ስላደረገ ነው። ሰይጣንን ከዓለም አላስወገደውም፣ ነገር ግን የኩነኔ መሳሪያው ከእጁ እስኪገፈፍ ድረስ ትጥቅ አስፈትቶታል።
ይቅር ስላልተባለ ኃጢአት አማኞችን መወንጀል አይችልም። ሊያጠፋን የሚችለው ብቸኛው ክስ ደግሞ ያ ነው። ስለዚህ፣ ወደ ፍፁም ጥፋት ሊያመጣን አይችልም። አካላችንን እና ስሜታችንን ሊጎዳ ይችላል –እንዲያውም ሊገድለን ይችላል። ሊፈትነን እና ሌሎችን በእኛ ላይ ሊያስነሳብንም ይችላል። ነገር ግን ሊያጠፋን አይችልም።
የቆላስይስ 2፥13–15 ወሳኝ ድል “ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረው የዕዳ መዝገብ” በመስቀል ላይ መቸንከሩ ነው። ዲያብሎስ ያንን መዝገብ፣ እኛን የሚወነጅልበት ዋና ነገሩ አድርጎት ነበር። አሁን ግን በገነት ችሎት የሚያቀርበው ክስ የለውም። በእኛ ላይ፣ አንድ፣ እጅግ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ አቅመ ቢስ ነው። እኛን መኮነን አይችልም። ክርስቶስ የኛን ፍርድ ተሸክሟል። ሰይጣንም ትጥቁን ተፈትቷል።
ይህ በሌላ አባባል በዕብራውያን 2፥14-15 ላይ አለ፦ “[ክርስቶስ ሰው ሆነ]፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።”
ሞት አሁንም ጠላታችን ነው። ነገር ግን ጥርሱ ተሰብሯል። የእባቡ መርዝ ተወግዷል። የሞት መንደፊያው የለም። የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበር። የኃጢአት የኩነኔ ኃይል ደግሞ በሕግ ጥያቄ ውስጥ ነበር። ነገር ግን የሕግን ፍላጎት ላረካው ክርስቶስ ምስጋና ይሁን። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥55)