መታደላችን በቃላት ሊገለጽ አይችልም | መስከረም 13

እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ …” አለው። (ዘፀአት 3፥14)

“እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ” የሚለው ታላቅ ስም፣ በልሕቀት ያለ፣ ፍጹምና ሁሉን እንደ ፈቃዱ የሚገዛው እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኛ መቅረቡን ያሳያል።

በዮሐንስ 8፥56-58 ላይ ኢየሱስ ለአይሁድ መሪዎች ትችት መልስ ይሰጣል። ኢየሱስ “’አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሤትም አደረገ’ አላቸው። አይሁድም፣ ‘ገና አምሳ ዓመት ያልሞላህ፣ አንተ አብርሃምን አይተሃል!’ አሉት። ኢየሱስም፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ’ አላቸው።”

ኢየሱስ ከዚህ በላይ የላቁ ቃላትን ሊናገር ይችል ነበር? ኢየሱስ፣ “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” ሲል የእግዚአብሔርን ስም፣ የማንነቱን ግርማ ሞገስ ለራሱ ሰየመ። በአገልጋይነት ትሕትናን ጠቅልሎ፣ ለዓመፃችን ሁሉ ማስተሰረያ ራሱን አቀረበ። ደግሞም ወሰን የሌለውን፣ ፍጹም፣ አንዳች የማይጎድለውን የእግዚአብሔርን ክብር ያለ ፍርሃት መመልከት እንድንችል መንገድ አዘጋጀልን።

በክርስቶስ ከእግዚአብሔር የተወለድን እኛ፣ ያህዌን (“እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ”) እንደ አባታችን ለማወቅ መታደላችን በቃላት ሊገለጽ አይችልም። ይህ አምላክ፦

– ያለ (የሚኖር)

– ማንነቱና ኃይሉ ለእርሱ ብቻ የሆነ

– የማይለወጥ

– የመላ ዓለሙ ኃይልና ጉልበት ከእርሱ የሆነ

– ፍጥረት ሁሉ ለእርሱ ሊገዛለት የተገባ አምላክ ነው።

ስሙን የሚያውቁ በእርሱ ይታመኑ (መዝሙር 9፥10)።