“ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)።
በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ የክርስቶስን ዋጋ እና ኀይል ማጉላት ነው። ክርስቶስን በሕይወታችን ማክበርና ከፍ ማድረግ ደግሞ የክርስቲያኖች ሁሉ የደስታ ጥግ ስለሆነ ይህ መከራ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ማለት ነው።
የጳውሎስ “የሥጋ መውጊያ” እንደማይወገድለት ጌታ ኢየሱስ ሲነግረው፣ እምነቱን ለመደገፍ ምክንያቱን ነግሮታል። “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)። ጳውሎስ ደካማ እንዲሆን እግዚአብሔር የወሰነው ክርስቶስ በጳውሎስ ቦታ ብርቱ ሆኖ እንዲታይ ነው።
ለራሳችን ብቁ እንደሆንን ከተሰማን፣ ክብሩን ክርስቶስ ሳይሆን እኛ እንወስዳለን። ስለዚህ “ማንም ሰው በእርሱ ፊት እንዳይመካ” ክርስቶስ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥29)። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ መለኮታዊ ኀይሉ በይበልጥ እንዲገለጥ ሲፈልግ፣ ብርቱ የሚመስሉ ሰዎችን ደካማ ያደርጋቸዋል።
ጳውሎስ ይህንን እንደ ጸጋ መቁጠሩን የምናውቀው በዚህ ደስ በመሰኘቱ ነው። “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9-10)።
በእግዚአብሔር ጸጋ በእምነት መኖር ማለት እግዚአብሔር በኢየሱስ ለእኛ በሆነው ነገር ሁሉ መርካት ማለት ነው። እምነትም እግዚአብሔር በኢየሱስ ለእኛ የሆነውን ሁሉ ከመግለጥና ከማጉላት ወደ ኋላ አያፈገፍግም። ድካሞቻችንና መከራዎቻችን ሁሉ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው።