ለእግዚአብሔር እና ለእውነት ያለ ጉጉት | ጥር 11

አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? ፈጽሞ አይሆንም! ሰው ሁሉ ሐሰተኛ፣ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“ ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ፣በፍርድም ፊት ረቺ ትሆናለህ።” (ሮሜ 3፥3-4)

ለእውነት የምንሰጠው ቦታ ያለ ጥርጥር ለእግዚአብሔር የምንሰጠውን ቦታ ያሳያል። በእርግጥ እግዚአብሔር ካለ እና የሁሉም ነገር ፈጣሪ አምላክ ከሆነ፣ የሁሉም ነገር መለኪያ እና ሚዛን እርሱ ነው ማለት ነው። እናም እርሱ ለነገሮች ሁሉ ያለው ዕሳቤ፣ የእኛ አስተሳሰብ እንዴት መሆን እንዳለበት የሚለካ ነው። እኛም ስለምንም ነገር ያለን ዐሳብ ሊመነጭ እና ሊመሠረት የሚገባው የእርሱ ዐሳብ ላይ ነው።

ለእውነት ግድ የለሽ መሆን፣ ለእግዚአብሔር ግድ የለሽ መሆን ነው። እግዚአብሔርን ከልብ መውደድ እውነትን ከልብ መውደድ ነው። እግዚአብሔርን የሕይወታችን መካከለኛ ማድረግ ማለት በአገልግሎታችን በእውነት መመራት ማለት ነው። እውነት ያልሆነ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እውነት የተፃፉ እነዚህን አራት ጥቅሶች አሰላስሉ፦

  1. እውነቱ እግዚአብሔር ነው

ሮሜ 3፥3-4 (እግዚአብሔር አብ)፦ “አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? ፈጽሞ አይሆንም! ሰው ሁሉ ሐሰተኛ፣ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን።”

ዮሐንስ 14፥6 (እግዚአብሔር ወልድ)፦ “ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ̔መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”

ዮሐንስ 15፥26 (እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ)፦ “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል።”

  1. እውነትን አለመውደድ ለዘላለም ያጠፋ

2ኛ ተሰሎንቄ 2፥10፦ ክፉዎች የሚጠፉት “እውነትን ባለመውደድ” ነው።

  1. ክርስና ሕይወት እውነትን በማወቅ ላይ የተመሠረተ ነው

1ኛ ቆሮንቶስ 6፥15-16፦ “ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ሴት ብልቶች ጋር አንድ ላድርገውን? ከቶ አይገባም! ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋር የሚተባበር ሰው ከእርሷ ጋር አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን?

  1. የክርስቶስ አካል የሚገነባው ፍቅር በተሞላ እውነት ነው

ቆላስይስ 1፥28፦ “እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን።” እግዚአብሔር ለራሱ እና ለእውነት ከልብ የምንጓጓ ያድርገን።