የጳውሎስ መዳን ለእናንተ ነበር | ሚያዚያ 29

ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ የነበርሁ ብሆንም፣ ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት እምነትና ፍቅር ጋርም የጌታችን ጸጋ ተትረፈረፈልኝ። …ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ። (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥13–1416)

የጳውሎስ መለወጥ (conversion) ለእናንተ ነው። ሰምታችሁኛል? ልድገምላችሁ፦ “ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።” አያችሁ፣ እዚህ ጋር እያወራ ያለው ስለ እኛ ነው — ስለ እናንተና ስለ እኔ።

ይህንን ሰምታችሁ የግላችሁ እንደምታደርጉት ተስፋ አደርጋለሁ። እግዚአብሔር ጳውሎስን መርጦ፣ በሉዓላዊ ጸጋው እንዲህ ባለ መንገድ ሲያድነው፣ ዛሬ ላይ ያላችሁትን እናንተን አስቀድሞ ተመልክቶ ነው።

ለዘላለም ሕይወት ኢየሱስን ካመናችሁ፣ ወይም ደግሞ ገና ልታምኑ ከሆነ፣ የጳውሎስ መለወጥ (conversion) ለእናንተ ነው። የእርሱ መለወጥ (conversion) ደግሞም የተለወጠበት መንገድ ዋና ምክንያት፣ የክርስቶስ አስደናቂ ትዕግስት ለእናንተ ጎልቶ ይታያችሁ ዘንድ ነው።  

ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት የነበረው ሕይወት፣ ለኢየሱስ ምን ያህል ረጅም ፈተና እንደነበረ አስታውሱ። በደማስቆ መንገድ ላይ “ለምን ታሳድደኛለህ?” ሲል ኢየሱስ ጠይቆታል (ሐዋርያት ሥራ 9፥4)። “ያለመታመንና የአመፃ ሕይወትህ ለእኔ ስደት ነው!” ይለዋል። ሆኖም ግን ጳውሎስ በገላትያ 1፥15 ላይ እግዚአብሔር ከመወለዱ አስቀድሞ ለሐዋርያነት እንደለየው ይነግረናል። ይህ እጅግ የሚደንቅ ነው። ጳውሎስ ከመለወጡ አስቀድሞ የኖረው መላ ሕይወቱ እግዚአብሔርን የመበደል ነበር። ከመወለዱ አስቀድሞ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠውን ኢየሱስን ሲቃወም እና ሲዘልፍ ነበር።

ለዚህም ነው ጳውሎስ፣ “የእኔ መለወጥ የኢየሱስን ትዕግስት አድምቆ ያሳያል” የሚለው። ዛሬም እያቀረበልን ያለው ይህንኑ ነው።

ኢየሱስ ጳውሎስን ያዳነበትን ጊዜና መንገድ የመረጠው ለእኛ ሲል ነው። ለእኛ “ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን” ያሳይ ዘንድ ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥16)። ስለዚህ ተስፋ አንቁረጥ። በእውነት ሊያድነን አይችልም ብለን አናስብ። ለቁጣ ያዘነበለ አድርገን አንየው። ከእርሱ በጣም ርቀን የሄድን አይምሰለን። በጣም የምንወደው ያላመነ ጓደኛችን በድንገት፣ ሳይታሰብ፣ ሉዓላዊ በሆነው፣ በተትረፈረፈው የኢየሱስ ጸጋ ሊለወጥ አይችልም ብለን አናስብ።