እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን | ታሕሳስ 10

“ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤
“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”

የሉቃስ ወንጌል 2፥12-14 (አ.መ.ት)

ሰላም ለእነማን? በመላእክቱ ውዳሴ ውስጥ ጠንከር ያለ እውነታ አለ። እግዚአብሔር ለወደዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን። እርሱ ለሚደሰትባቸው ሰዎች ሰላም ይሁን። ነገር ግን ያለ እምነት እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም (ዕብራውያን 11፥6)። ስለዚህም የገና በዓል ለሁሉም ሰው ሰላምን ሊያመጣ አይችልም።

ፍርዱም ይህ ነው” አለ ኢየሱስ፤ “ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ(ዮሐንስ 3፥19)። ወይም ደግሞ በዕድሜ ያረጀው ስምዖን ሕፃኑን ኢየሱስን ሲመለከት የተናገረው፣ “እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል…”(ሉቃስ 2፥34-35)። ብዙዎች የገና በዓልን ሊቃወሙት እንደሚገባ ምልክት አድርገው ይመለከቱታል!

የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐንስ 1፥11-12)። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ብቻ ነበር እንደዚህ ያለው፦ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” (ዮሐንስ 14፥27)።

አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የእግዚአብሔርን ሰላም ተቀብለው ሊደሰቱበት የሚችሉት፣ በነገር ሁሉ በጸሎት እና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናቸውን ለእግዚአብሔር የሚያስታውቁት ናቸው (ፊልጵስዩስ 4፥6-7)።

የእግዚአብሔርን የሰላም ሀብት ካዝና መክፈቻ ቁልፉ፣ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ያለ እምነት ነው። ስለዚህም ጳውሎስ ሲጸልይ እንዲህ ይላል፤ “የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ” (ሮሜ 15፥13)። በዚህም መሠረት፣ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል በማመናችን ደስታን፣ ሰላምንና ፍቅርን ስንሞላ፣ ያኔ እግዚአብሔር ይከብራል።

ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን! ለሁሉም ሕዝብ፣ ነገድ፣ ወገን፣ እና ቋንቋ! ለሚያምኑ ሁሉ!