በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም። ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል… ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ። (ዮሐንስ 15፥7-8፣ 11)
ጸሎት ከኢየሱስ ጋር ከሚኖር ፍሬያማ ሕብረት የተነሣ የሚገኘውን ሐሴት የምንፈልግበት መንገድ ነው። እግዚአብሔርም በጸሎት መልስ ምክንያት በሚመጣው እድገት እንደሚከብር እናውቃለን። ታዲያ ለምንድን ነው የእግዚአብሔር ልጆች ቀጣይነት ያለው ፍሬያማ ጸሎት መጸለይ የሚከብዳቸው?
ይህ የሚሆንበት ምክንያት ፍላጎቱ ስለሌለን ሳይሆን ለዚህ የሚሆን ዕቅድ ስለማንነድፍ ይመስለኛል።
የአራት ሳምንት ጉብኝት ማድረግ ብትፈልጉ ድንገት አንድ ቀን ተነሥታችሁ እንሂድ አትሉም። ምንም የተዘጋጀ ነገር አይኖራችሁም፤ የት እንደምትሄዱም አታውቁም፤ የታቀደ ነገር የለም። አብዛኞቻችን ጸሎትን እንደዚህ ነው የምናየው። ሁልጊዜ እየተነሣን የበለጠ መጸለይ እንዳለብን እናስባለን ግን ዕቅድ የለንም።
የት መሄድ እንዳለብን አናውቅም። ዕቅድ የለም፤ ጊዜና ቦታም የለም። ዕቅድ አልባ መሆን ደግሞ ጥልቅ የሆነ የፀሎት ልምምድ እንዳይኖረን ያደርጋል። የጉዞ ዕቅድ ከሌላችሁ ያላችሁ አማራጭ ቤታችሁ ቁጭ ብላችሁ ቴሌቪዥን መመልከት ነው። ያልታቀደ መንፈሳዊ ሕይወትም እንዲሁ ወደ ቡዘና መቀመቅ የሚንደረደር ሕይወት ነው። ልንሮጠው የሚገባ ሩጫ፣ ልንጋደለውም የሚገባን ገድል አለ። በፀሎት ሕይወታችሁ መታደስን ከፈለጋችሁ፣ ይህንን ለማየት እቅድ ሊኖራችሁ ይገባል።
ስለዚህ እኔ የማቀርበው ቀለል ያለ ሐሳብ ይህ ነው። ዛሬውኑ ቅድሚያ ስለ ምንሰጣቸው ነገሮች እና ጸሎት በዚያ ውስጥ ስላለው ቦታ እናስብ። አዲስ ውሳኔ ይኑረን፤ ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ግንኙነት ይኑረን፤ ጊዜ እና ቦታ እንወስን፤ የሚመራን የእግዚአብሔር ቃል ይኑረን።
በተጨናነቀ ጊዜያችሁ ምክንያት አትሸበሩ። ሁላችንም በሕይወታችን የምናስተካክለው ነገር አለ። ለእግዚአብሔር ክብር እና ለደስታችሁ ሙላት ይሆን ዘንድ የዛሬዋን ቀን ወደ ፀሎት የመመለሻ ቀን አድርጓት።