እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤ ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ (መዝሙር 67፥3፣ 5)።
እግዚአብሔር ከእኛ ምስጋናን የሚፈልገው ወይም የሚያዝዘው ለምንድን ነው?
ሲ. ኤስ. ሊዊስ የተባለው ብሩህ ጸሐፊ እንዲህ ይላል፦
ሰዎች ማንኛውንም ዋጋ የሚሰጡትን ነገር በፈቃዳቸው ያወድሳሉ። ከራሳቸውም አልፈው እኛም አብረናቸው እንድናወድስ ይፈልጋሉ። “እዩዋት እስኪ፣ አታምርም? ይሄስ ገራሚ አልነበረም? አያስደንቀም ይሔስ?” በማለት አግራሞታቸውን ያጋራሉ።
ዘማሪዎቹም እያደረጉ ያሉት ይህንን ነው። ሁሉም ሰው የሚያደንቀው ነገር እንዲደነቅለት እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እነርሱም የሚወዱት እና ዋጋ የሚሰጡት ነገር እንዲደነቅላቸው ያውጃሉ። እግዚአብሔርን ማመስገን በጣም ይከብደኝ የነበረበት ዋነኛው ምክንያት፣ ይህንን ለሌላ ተራ ነገር ሁሉ የምናደርገውን ነገር፣ ከሁሉ ሊልቅ ለሚገባው ደስታ እና እርካታ ማድረጋችንን በሞኝነት እቃወም ስለነበር ነው።
የምንደሰትበትን ነገር ማወደስ የሚያስደስተን ምክንያቱ፣ ውዳሴው መደሰታችንን ከመግለጥ ባለፈ ደስታዉን ሙሉ ስለሚያደርገው ነው፤ የታሰበውም እንዲያ እንዲሆን ነው። ፍቅረኛሞች ያለማቋረጥ አንዱ ለሌላው ቁንጅናቸውን የሚናገሩት እንዲያው ለመሞጋገስ ሳይሆን፣ ደስታው ካልተገለጸ ሙሉ ስለማይሆን ነው።
እግዚአብሔር ምስጋናን አምጡ የሚለው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ይሄ ነው። ልንደሰት ከምንችለው ደስታ ሁሉ የላቀው ደስታችን የሚገኘው እርሱን በማወደስ ውስጥ ነው! የሚያስደስተንን ነገር የምናወድስበት ምክንያቱ፣ ደስታው በምስጋና ካልተገለጸ ሙሉ ሊሆን ስለማይችል ነው። ዋጋ ስለምንሰጠው ነገር መናገር ካልቻልን፣ የምንወደውን ነገር ማወደስ ከተከለከልን፣ እና የምናደንቀውን ነገር ማመስገን ካልተፈቀደልን፣ ደስታችን እንዴት ሙሉ ሊሆን ይችላል?
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ከወደደን፣ ደግሞም ደስታችንን ሙሉ ለማድረግ ከፈቀደ፣ ሊሰጠን የሚገባው ራሱን ብቻ አይደለም፤ የልባችንን ተገዢነት እና ምስጋና ከእኛ ሊቀበል ይገባዋል። ይህም ደግሞ እርሱ አንዳች የምስጋና እጥረት ወይም የሚያካክሰው ድካም ስላለበት ሳይሆን፣ ስለሚወድደን እና ከፍጥረት ሁሉ የሚልቀውን እርሱን በማወቅ እና በማመስገን ብቻ የሚገኘውን የደስታችንን ሙላት ስለሚፈልግ ነው።
እግዚአብሔር በእውነት ስለእኛ የሚቆም ከሆነ ለራሱ ክብር መቆም አለበት! በዓለማት ሁሉ፣ የራሱን ክብር መፈለጉ ትዕቢት ሳይሆን ከፍተኛ የፍቅር ተግባር የሚሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። ራሱን ማክበሩ ከሁሉ በላቀ መልኩ የበጎነቱ መገለጫ ነው። ነገሮችን ሁሉ “ለክብሩ ምስጋና” ሲያደርግ፣ በመላው ዓለም ውስጥ ናፍቆታችንን ሊያረካ የሚችለውን ብቸኛ ነገር ይጠብቅልናል፣ ሳይሰስትም ይሰጠናል (ኤፈሶን 1፥12፣ 14)።
እግዚአብሔር ስለእኛ ይቆማል! ይወግንልናል! የዚህ ፍቅር መሠረቱ ደግሞ እግዚአብሔር ድሮም፣ አሁንም ለዘላለምም ለራሱ ክብር መሥራቱ ነው።