እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዞቹን መፈጸም ነውና። ትእዛዞቹም ከባድ አይደሉም፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው? (1ኛ ዮሐንስ 5፥3-5)
በዚህ ክፍል ላይ ግልፅ ሆኖ የምንመለከተው ነገር፣ ከእግዚአብሔር ዳግም መወለድ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንደሸክም ከመመልከት ይልቅ ደስ እንድንሰኝባቸው እንደሚያደርገን ነው። ታዲያ ግን ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
እንዴት ነው ከእግዚአብሔር መወለድ የእርሱን ትእዛዛት ሸክም ከመሆን ይልቅ ወደ ደስታ የሚቀይረው?
ሐዋሪያው ዮሐንስ ሲናገር፣ “ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው” ይላል (1ኛ ዮሐንስ 5፥4)። በሌላ አነጋገር፣ ከእግዚአብሔር መወለድ ትዕዛዞቹን በእምነት እንድናሸንፍ ያደርገናል ማለት ነው። ይህ እውነትም በ1ኛ ዮሐንስ 5፥1 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፦ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል።”
እምነት ከእግዚአብሔር ለመወለዳችን ማረጋገጫ ነው። ዳግመኛ የምንወለደው ለማመን በመወሰን አይደለም። እግዚአብሔር እኛን ዳግም በመውለድ፣ የማመን ፍላጎትን በውስጣችን ይፈጥርልናል። ጴጥሮስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ እንዳለው፣ “እርሱ … ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት … እንደ ገና ወለደን” (1ኛ ጴጥሮስ 1፥3)። ሕያው ተስፋችን እና ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ ያለን እምነት፣ እግዚአብሔር እኛን ዳግም በመውለድ ውስጥ የሚሰራው ሥራ ነው።
ስለዚህ ዮሐንስ፣ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል”፣ እንዲሁም “ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው” ሲል፣ እግዚአብሔር በአዲስ ልደት ዓለማዊ የሆነ አለመታዘዛችንን እንድናሸንፍ ያስችለናል ማለቱ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፥4)። ዳግም ልደት እምነትን በመፍጠር ይህንን ያሳካል። ይህም እምነት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንደሸክም ከመመልከት ይልቅ ደስ እንድንሰኝባቸው ያደርገናል።
ለእግዚአብሔርና ለፈቃዱ ያለንን ተፈጥሮአዊ ጠላትነት አሸንፎ፣ ትእዛዛቱን እንድንጠብቅና ከመዝሙረኛውም ጋር አብረን “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” እንድንል የሚያደርገን፣ እምነት ብቻ ነው (መዝሙር 40፥8)።