እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።’ (ማቴዎስ 6፥9)
እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የሚያደርገው “ለስሙ ሲል” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይናገራል።
- ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። (መዝሙረ ዳዊት 23፥3)
- ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ ። (መዝሙረ ዳዊት 25፥11)
- ስለ ስሙ አዳናቸው። (መዝሙረ ዳዊት 106፥8)
- ስለ ስሜ ስል ቍጣዬን አዘገያለሁ። (ኢሳይያስ 48፥9)
- ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና። (1ኛ ዮሐንስ 2፥12)
በእነዚህ ሁሉ እና በመሳሰሉት ክፍሎች ውስጥ የእግዚአብሔርን ልብ የሚነካው ምን እንደሆነ ከጠየቃችሁ፣ መልሱ፦ እግዚአብሔር ስሙ እንዲታወቅና እንዲከበር በማድረግ ይደሰታል የሚል ነው።
ሊጸለይ የሚችለው የመጀመሪያውና ዋነኛው ጸሎት “ስምህ ይቀደስ” የሚለው ነው። ይህ አድናቆት ነው ብዬ አስብ ነበር። “ሃሌ ሉያ! የጌታ ስም የተቀደሰ ነው!” እንዲሚለው ዓይነት። ነገር ግን አድናቆት አይደለም። ልመና ነው። እንደውም አስገዳጅ ትዕዛዝ ነው። ጌታ ሆይ፣ ይሁን! እንዲሆን አድርገው። ስምህ የተቀደሰ ይሁን። ይህ ልመናዬ ነው፣ ጸሎቴ ነው። ይህንን እንድታደርግ አጥብቄ እለምንሃለሁ፦ ሰዎች ስምህን እንዲቀድሱ አድርግ። እኔም ራሴ፣ ስምህን እንድቀድስ አድርገኝ እያልነው ነው።
እግዚአብሔር ስሙን “የሚቀድሱ” ብዙ ሰዎች ሲኖሩት ደስ ይለዋል። ለዚህም ነው ልጁ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲጸልዩ ያስተማራቸው። በእርግጥም ኢየሱስ የመጀመሪያውና ዋነኛው ጸሎት አድርጎታል። ምክንያቱም ይህ የአብ የመጀመሪያና ትልቁ መሻቱ ነው።
“ጌታ ሆይ፣ ስምህን የሚቀድሱ ሰዎችን አብዛ” ማለት ብዙ ሰዎች ስምህን እንዲያከብሩ፣ እንዲያደንቁ፣ ክብር እንዲሰጡ፣ ዋጋ እንዲሰጡ፣ አክብሮታቸውን እንዲገልጹ፣ እንዲፈሩና እንዲያወድሱ አድርግ ማለት ነው። የሚያወድሱህ ሰዎች ቁጥራቸው ዕለት ዕለት ይብዛ! ታዲያማ ይህ ፀሎት፣ ወንጌል እንዲሰፋ የሚጓጓ የሚስዮናዊ ሰው ጸሎት መሆኑን መመልከት ትችላላችሁ።