“ጌታ ሆይ . . . መጸለይን አስተምረን።” (ሉቃስ 11፥1)
እግዚአብሔር የሚመልሰው የፍጹማንን ጸሎት ሳይሆን የኃጢአተኞችን ነው። እናንተም መስቀሉ ላይ በማተኮር ይህንን ካላስተዋላችሁ በጸሎት ሕይወታችሁ ፍጹም ሽባ ሆናችሁ ልትቀሩ ትችላላችሁ።
በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የራሳቸው ኃጢአት ችግርን አምጥቶባቸው፣ ይድኑ ዘንድ የሚጮኹትን ኃጢአተኛ ህዝቡን ጩኸት እግዚአብሔር ሲሰማ የሚያሳዩ በርካታ ክፍሎችን መጥቀስ እንችላለን (መዝሙር 38፥4፣ 15፤ 40፥12–13፤ 107፥11–13)። ነገር ግን ከሉቃስ 11 ላይ በሁለት መንገድ እንመልከት፦
በሉቃስ 11፥2-4 ላይ ባለው የጌታችን ጸሎት፣ ኢየሱስ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ …” በማለት ይጀምራል። ከዚያም በቁጥር 4 ላይ፣ “ኃጢአታችንንም ይቅር በለን” የሚለውን ልመና ያካትተዋል። ስለዚህ፣ የጥቅሱን መጀመሪያ መካከል ላይ ካለው ልመና ጋር ካገናኛችሁት፣ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ… ኃጢአታችንን ይቅር በለን” እያለ እንደሆነ ትረዳላችሁ።
ልክ “ስምህ ይቀደስ” እንደሚለው ጸሎት ሁሉ፣ ይህም ልመና የጸሎታችን ዋና አካል መሆን እንዳለበት እያስተማረን ነው። በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ ንስሓ መግባት እና ይቅርታ መጠየቅ እንደሚያስፈልገን ኢየሱስ ይነግረናል።
በሌላ አነጋገር፣ ሁሌም ኃጢአተኞች ነን። ከምናደርገው ነገር አንዱም ፍጹም አይደለም። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተሐድሶ ካመጡት አባቶች ዋነኛ የሆነው ማርቲን ሉተር፣ በመጨረሻዎቹ የሞቱ ሰዓታት እንደተናገረው፣ “ሁላችንም ለማኞች መሆናችን እውነት ነው።” ለጸሎት ከመቅረባችን በፊት በተወሰነ መልኩ ለእግዚአብሔር ታዝዘን እንኳ ቢሆን፣ ሁላችንም ወደ ጌታ ስንመጣ ሁልጊዜ ኃጢአተኞች ሆነን ነው። እግዚአብሔርም እንዲህ ወደ እርሱ የሚጸልዩ ኃጢአተኞችን ጸሎት ችላ አይልም።
በሉቃስ 11፥13 ላይ የምናየው ሁለተኛው ክፍል ይህ ነው፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ክፉዎች” ብሎ ይጠራቸዋል። ከበድ ያለ ቃል ነው። ይህንን ሲል ከእርሱ ጋር ኅብረት አልነበራቸውም ማለቱ አይደለም። ወይም ጸሎታቸው ሊመለስ አይችልም እያለም አልነበረም።
እያለ ያለው፦ በዚህ በወደቀ ዘመን ውስጥ እስከኖሩ ድረስ፣ የገዛ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ ሳይቀሩ፣ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ በክፋት የተበከለ ነው፣ ነገር ግን በጸጋው እና በኃይሉ ላይ የሚታመኑ ከሆነ፣ ብዙ መልካም ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ ነው።
ሁላችንም፣ በተመሳሳይ ቅጽበት፣ ክፉዎችና የተቤዠን ነን። ቀስ በቀስ ክፋታችንን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እያሸነፍን ነው። ነገር ግን በኀጢአት ምክንያት የመጣብን መሠረታዊ የሆነ ውድቀት አማኝ በመሆን ብቻ አይጠፋም።
ኃጢአተኞች እና ለማኞች ነን። እናም ኃጢአተኝነታችንን ካወቅን፣ ከካድን፣ ከተዋጋን፣ እና የክርስቶስ መስቀል ብቸኛው ተስፋችን እንደሆነ በማመን የሙጥኝ ካልን፣ ያኔ እግዚአብሔር ይሰማናል፤ ጸሎታችንንም ይመልሳል።