“በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።” (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)
ጸሎት የተስፋ ቃሎች እና ወደ ፊት የሚገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ማረጋገጫ መልስ ነው።
ጸሎት እግዚአብሔር ካከማቸው ጸጋ የምንካፈልበት መንገድ ነው።
ጸሎት እንዲሁ በጨለማ ውስጥ ጥሩ የሚያስብልን እግዚአብሔር እንዳለ ተስፋ ማድረግ አይደለም። ጸሎት በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ላይ ይተማመናል፤ እግዚአብሔር ካከማቸው ጸጋም በየዕለቱ እንደሚያስፈልገው ይካፈላል።
በዚህ ወሳኝ ጥቅስ ሁለት ክፍሎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዳያመልጣችሁ። በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በክርስቶስ ነው፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው “በዚህ ምክንያት ነው።”
በደንብ እንድንረዳው ሁለቱን ዐረፍተ ነገሮች እንገልብጣቸው። ስንጸልይ፣ በክርስቶስ ለእግዚአብሔር አሜን እንላለን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለተስፋ ቃሎቹ ሁሉ በክርስቶስ የተረጋገጠ አሜን ብሏል። ጸሎት እግዚአብሔር ለክርስቶስ ሲል ቃል የገባውን በጸጋው እንዲፈጽም መለመን ነው። ጸሎት በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ያለንን እምነት መሠረቱ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያገናኘዋል።
ወደ መጨረሻው ነጥብ ስናመራ፣ “አሜን” በጸሎት ጊዜ ሙሉና ውድ የሆነ ቃል ነው። “አዎን፤ ይህን ጸሎት እጸልያለሁ” ማለት ሳይሆን “አዎን፤ እግዚአብሔር እነዚህን የተስፋ ቃሎች ሁሉ ፈጽሟል” ማለት ነው።
አሜን ማለት “አዎን ጌታ ሆይ አንተ ታደርገዋለህ” ማለት ነው። “አዎን ጌታ ሆይ ኅይለኛ ነህ፤ አዎን ጌታ ሆይ ጥበበኛ ነህ፤ አዎን ጌታ ሆይ መሐሪ ነህ፤ አዎን ጌታ ሆይ ሁሉም የወደ ፊቱ ጸጋ ከአንተ የሚመጣ እና በክርስቶስ የተረጋገጠ ነው” ማለት ነው።
“አሜን” የተስፋ ማረጋገጫ እና ለተስፋ ስንጸልይ ሙሉ መተማመናችንን የምንገልጽበት ቃል ነው።