የጸሎት ቀዳሚ አጀንዳ | ጥቅምት 14

“እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” (ማቴዎስ 6፥9)

በጌታችን ጸሎት ላይ ኢየሱስ ስንጸልይ ማስቀደም ያለብን በሰማይ የሚገኝውን የአባታችንን ስም መቀደስ መሆኑን ይነግረናል። በእኛ፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በዓለም፣ በሁሉም ቦታ።

ይህ ልመና መሆኑን አስተውሉ። አዋጅ፣ ትዕዛዝ ወይም የውዳሴ መግለጫ አይደለም፤ ልመና ነው። ለዓመታት የጌታ ፀሎት በምሥጋና የሚጀምር ይመስለኝ ነበር፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ”። ነገር ግን አዋጅ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የራሱ ስም መቀደሱን እንዲመለከት የቀረበ ልመና ነው።

ይህ እንደ ማቴዎስ 9፥38 ነው። ኢየሱስ “የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት” ሲል ሁሌ ይገርመኛል። ከእኛ ይልቅ እርሻውን በሚገባ የሚያውቀው የእርሻው ባለቤትን፣ ሌሎች የሚሠሩ እጆችን እንዲልክ እንድንጠይቀው ታዘናል።

ታዲያ የጌታ ጸሎት ላይም ተመሳሳይ ነገር አይደል የምናገኘው? ኢየሱስ ለስሙ ቀናተኛ የሆነውን እግዚአብሔርን የራሱ ስም መቀደሱን (መከበሩን፣መፈራቱን እና ከፍ ማለቱን) እንዲመለከት እንድንጠይቀው ይነግረናል።

ይህ ሊያስገርመን ይችላል። ነገር ግን ተጽፎ እናየዋለን። ሁለት ነገሮችንም ያስተምረናል።

  1. ጸሎት እግዚአብሔር ማድረግ የማይፈልጋቸውን ነገሮች እንዲያደርግ አያስገድደውም። የእርሱ ዋና ፍላጎት ስሙ መቀደሱ ነው። ከዚህ በላይ የሚሻው ነገር የለም። ነገር ግን እኛ ይህንን ራሱ እንዲያደርግ እንጠይቀዋለን።
  2. ሌላው ጸሎት እግዚአብሔር የሚያስቀድማቸውን ነገሮች ከእኛ ፍላጎቶች ጋር የሚያስታርቅበት መንገድ ነው። ጸሎቶቻችን ከታላቁ አጀንዳው የሚነሱ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ታላቅ የሆኑ ነገሮችን ያደርጋል።

ልባችሁን ከእግዚአብሔር ቅንዓት እና ለስሙ መቀደስ ካለው ፍላጎት ጋር ስታዛምዱ እጅግ የተሻለ ጸሎት ትጸልያላችሁ። የመጀመሪያ ጸሎታችሁ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ሲሆን፣ እግዚአብሔር ለስሙ ባለው ቅንዓት ከሚፈልቀው ኅይል ተካፋይ ትሆናላችሁ።