“ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፣ አዳኜና አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁ።” (መዝሙር 42፥11)
በመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚያጋጥመንን ተስፋ መቁረጥ መዋጋት መማር አለብን። ውጊያው ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ በመታመን የሚደረግ የእምነት መጋደል ነው። የምንጋደለውም ስለ እግዚአብሔር ማንነት እና ወደፊት ስለሚገለጠው ተስፋ ለራሳችን በመስበክ ነው።
መዝሙረኛው በመዝሙረ ዳዊት 42 ላይ ያደረገው ይህንኑ ነው። ለታወከችው ነፍሱ ይሰብካታል። ራሱን ይወቅሳል፣ ደግሞም ከራሱ ጋር ይሟገታል። ዋና ሙግቱም ወደፊት የሚመጣው ጸጋ ነው፦ “ተስፋሽን በእግዚአብሔር ላይ አድርጊ! እግዚአብሔር ወደፊት የሚሆንልሽን እመኚ። የምስጋና ቀን እየመጣ ነው። የጌታ መገኘት ረዳትሽ ይሆናል። እርሱም ከእኛ ጋር ለዘላለም እንደሚኖር ቃል ገብቷል” በማለት ለነፍሱ ይነግራታል።
እውቁ እንግሊዛዊ ሰባኪ ዶ/ር ማርቲን ሎይድ-ጆንስ፣ መንፈሳዊ ድባቴን ለማሸነፍ ወደፊት ስለሚገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ለራስ መስበክ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። Spiritual Depression በተሰኘው እጅግ ጠቃሚ መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
በሕይወታችሁ ደስተኛ የማትሆኑበት ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ለራሳችሁ ከመንገር ይልቅ ራሳችሁን ስለምታደምጡ እንደሆነ አስተውላችኋል? በማለዳ ከእንቅልፋችሁ ከነቃችሁበት ቅጽበት ጀምሮ ወደ እናንተ የሚመጡ ሃሳቦች አሉ። እናንተ ፈልጋችሁ አላመጣችኋቸውም፤ ነገር ግን ያንሾካሹካሉ፤ የትናንቱን ችግር መልሰው ያመጡታል … ልክ የሆነ ሰው እንደሚያወራችሁ፣ ራሳችሁ ከራሳችሁ ጋር እያወራ ነው። በመዝሙር 42 ላይ ያለው ይህ ሰው ግን ራሱን እንዲያነጋግረው ከመፍቀድ ይልቅ ለራሱ መንገርን ጀመረ። “ነፍሴ ሆይ ለምን ትተክዣለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል። ነፍሱ እያስጨነቀችው ነበር። እናም ተነሥቶ እንዲህ ይላታል፦ “ነፍሴ፣ ለአፍታ አዳምጪ። እኔ እነግርሻለሁ።” (20–21)
ከተስፋ መቁረጥ ጋር የሚደረገው ትግል የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ለማመን የሚደረግ ትግል ነው። በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ማመን የሚመጣው ደግሞ ቃሉን በመስማት ነው። ስለዚህም የእግዚአብሔርን ቃል ለራሳችን መስበክ ትግሉን ለማሸነፍ ዋነኛው መሣሪያ ነው።