መንገዱን አቅኑ | ታሕሳስ 5

ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።

የሉቃስ ወንጌል 1፥16-17

መጥምቁ ዮሐንስ ለእስራኤል የሠራውን ሥራ፣ የገና ወቅትም ለእኛ ሊሠራልን ይችላል። በዚህ ዓመት ሳትዘጋጁ የገና በዓል እንዳይደርስባችሁ። ይህንን ስል፣ መንፈሳዊ በሆነ መዘጋጀት ሳትዘጋጁ እንዳይደርስባችሁ ማለቴ ነው። የኢየሱስ የልደት በዓልን በመንፈሳዊ ዝግጅት ተዘጋጅታችሁ ካከበራችሁት፣ ደስታችሁም ሆነ ውጤቱ ዕጥፍ ድርብ ይሆናል!

ስለዚህ፣ ትዘጋጁ ዘንድ…

አንደኛ፣ ምን ያህል አዳኝ እንደሚያስፈልገን አሰላስሉ። የልደት በዓል ታላቅ ደስታ ከመሆኑ በፊት የክስ ደብዳቤ ነው። “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃስ ወንጌል 2፥11)። አዳኝ ባያስፈልጋችሁ ኖሮ፣ ኢየሱስ መወለዱም ሆነ የልደት በዓል ባላስፈለገ ነበር። የሚያድነን አዳኝ ምን ያህል እንደሚያስፈልገን እስካልተረዳን ድረስ የልደት በዓል የተፈለገውን ያህል ፍሬ አያፈራም። እነዚህ አጫጭር የገና ሰሞን ጥሞናዎች፣ ስለ አዳኝ አስፈላጊነት በልባችሁ ውስጥ ጣፋጭም መራራም ስሜት ይፍጠሩባችሁ።

ሁለተኛ፣ በሰከነ መንገድ ራሳችሁን መርምሩ። የአርባ (ሁዳዴ) ፆም ለፋሲካ በዓል እንደሆነው ሁሉ የገና ወር ለኢየሱስ ልደት ነው። “አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ” (መዝሙረ ዳዊት 139፥23-24)። እያንዳንዱ ልብ ቤቱን በማጽዳት ለጌታ ክፍል ያዘጋጅለት!

ሦስተኛ፣ እግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ጉጉት፣ ናፍቆት፣ እና መነቃቃት ቤታችሁን ይሙላ! በተለይ ደግሞ ልጆች ካሏችሁ፣ እናንተ ለክርስቶስ ጉጉታችሁ ከጨመረ፣ እነርሱም ይከተሏችኋል። ሆኖም ግን የልደት በዓልን ምድራዊ በሆኑ ዕቃዎች ብቻ ካከበርነው፣ ልጆቻችን እንዴት እግዚአብሔርን ይጠማሉ? የንጉሡ መምጣት በልጆቻችሁ በግልጽ ይታወቅ ዘንድ አስተሳሰባችሁን አስፉት!

አራተኛ፣ ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላችሁ በማጥናት እና በመሸምደድ ራሳችሁን ቃሉ ውስጥ ንከሩ! “በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር” (ትንቢተ ኤርሚያስ 23፥29)። በበረዶ ወቅት ሰዎች በእሳት ዙሪያ ክብ ሰርተው እንደሚሞቁ፣ እናንተም በዚህ በጸጋ ቀለማት ባሸበረቀው የልደት ወር ዙሪያ ተቀምጣችሁ እንድትሞቁ ትጋበዛላችሁ! ለሺህ ስብራቶች በዚያ ፈውስ አለ። ለድቅድቅ ሌሊቶች ብርሃን ይሆናል።