መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ። (ኢሳይያስ 57፥18)
የምታምኑትን አስተምሮአችሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተማሩ። መንፈሳችሁን የሚመግበውና የሚሻለው መንገድ እርሱ ነው።
ለምሳሌ፣ እንቢ ስለማይባለው የጸጋ አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተማሩ። ይህንን ስታደርጉ፣ ጸጋ እንቢ ሊባል አይችልም እያለ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ከመረጠ እንቢታችንን ማሸነፍ ይችላል፣ ደግሞም ያሸንፋል ማለት እንደሆነ ትረዳላችሁ።
ለምሳሌ፣ በኢሳይያስ 57፥17-19፣ እግዚአብሔር ዐመፀኛ ሕዝቡን ቀጥቶ ፊቱን ሲያዞርባቸው እናያለን፦ “ኀጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቍጣ ከእርሱ ሸሸግሁ” (ቁጥር 17)።
ነገር ግን በንሰሀ አልተመለሱም። ይልቁኑ፣ ከእርሱ መሸሻቸውን ቀጠሉበት። እንቢ አሉ፦ “ያም ሆኖ በገዛ መንገዱ ገፋበት” (ቁጥር 17)።
ስለዚህ ጸጋን መቃወም ይቻላል። እንደውም እስጢፋኖስ የአይሁድን መሪዎች፣ “መንፈስ ቅዱስን ሁል ጊዜ ትቃወማላችሁ” ይላቸዋል (ሐዋርያት ሥራ 7፥51)።
ታዲያ እግዚአብሔር በመቀጠል ምን አደረገ? የሚቃወሙትን ወደ ንሰኀ እና ሙሉነት ሊያመጣ ኃይል የለውምን? በፍጹም። ኃይል አለው። ቀጣዩ ቁጥር፣ “መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ” ይላል (ኢሳይያስ 57፥18)።
ስለዚህ፣ ጸጋን የሚቃወመውንና እንቢተኛውን እግዚአብሔር “እፈውሰዋለሁ” ይላል። እርሱ “ይመልሳል”። “መመለስ” የሚለው ቃል “ሙሉ ወይም ፍጹም ማድረግ” ማለት ነው። ሻሎም ከሚለው ቃል ጋር ይመሳሰላል – “ሰላም”። እግዚአብሔር ጸጋ ተቃዋሚውን ሰው እንዴት እንደሚመልስ በሚያስረዳው ቀጣዩ ቁጥር ላይ ያ ሙሉነትና ሰላም ተጠቅሷል።
እንዴት አድርጎ ይመልሰዋል? “’በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም (ሻሎም፣ ሻሎም) ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ’ ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳይያስ 57፥19)። እግዚአብሔር የሌለን ነገር ይፈጥራል – ሰላምና ሙሉነት ያመጣል። የዳንነው እንዲህ ነው። ወደ ኋላ ከመንሸራተት በተደጋጋሚ የተመለስነውም እንዲሁ ነው።
የእግዚአብሔር ጸጋ ምስጋናን ባልነበረበት ፈጥሮ የእኛን ተቃውሞ ያሸንፋል። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላምንና ሙሉነትን ያመጣል። ይህንንም ደግሞ በ“መመለስ” ያደርገዋል። የተቃውሞን በሽታ በታዛዥነት መድኃኒት ያክመዋል።
እንቢ የማይባለው ጸጋ ዋና ሃሳቡ መቃወም አይቻልም ማለት አይደለም። መቃወም እንችላለን፤ ደግሞም እንቃወማለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ሲመርጥ፣ ተቃውሟችንን አሸንፎ በመገዛት መንፈስ ይመልሰናል ማለት ነው። እርሱ ይፈጥራል። “ብርሃን ይሁን” ይላል። እርሱ ያድናል። እርሱ ይመራል። እርሱ ይመልሳል። እርሱ ያጽናናል።
ስለዚህም ከዓመጻችን እና ከመንሸራተታችን በመመለሳችን አንመካም። በጌታችን ፊት በመውደቅና በደስታ በመንቀጥቀጥ ዓመጸኛነታችንን ላሸነፈው እንቢ ስለማይባለው ጸጋው እናመሰግነዋለን።