ቴብል ቶክ፦ ወደ ክርስትና እምነት እንዴት ልትመጣ ቻልክ? ጌታ ከ ዘ ናቪጌተርስ ጋራ እንድታገለግል የጠራህስ እንዴት ነው?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ያደግሁት በየእሑዱ ላላመኑት ሰዎች ጌታን የመቀበል የመድረክ ጥሪ በሚደረግበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። በ9፣ 11 እና 13 ዓመቴ ለውሳኔ ወደ ፊት የወጣሁ ቢሆንም፣ ዳግም አልተወለድሁም ነበር። በመጨረሻም፣ በ18 ዓመቴ፣ በዐልጋዬ ላይ ለብቻዬ ሳለሁ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ምንም ይሁን ምን፣ ኢየሱስ አዳኜ እንዲሆን እፈልጋለሁ።” ወዲያውኑ የድነቴን ዋስትና አገኘሁ።
በኮሪያ ጦርነት ወቅት በባሕር ኀይል ውስጥ ሳገለግል፣ በሌላ የባሕር ኀይሉ መኮንን በኩል ዘ ናቪጌተርስን ተዋወቅሁ፤ እናም በደቀ መዝሙርነት መርሐ ግብራቸው አማካይነት በመንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ጀመርሁ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ሳለሁ፣ በክፍለ ምንባቡ ውስጥ ያለ አንድ ነገር፣ “ከ ዘ ናቪጌተርስ ጋራ ለማገልገል ፈቃደኛ እሆናለሁ?” ብዬ እንድጠይቅ አደረገኝ፡፡ ከዚያ ብዙም ሳይቈይ፣ አካላዊ ፈተናን ወደቅሁ፤ እናም ከስድስት ወራት በኋላ በጤና እክል ምክንያት ተሰናበትሁ። በዚያን ጊዜ፣ የ ዘ ናቪጌተርስ አመራር በሳን ዲዬጎ ውስጥ ሠልጣኝ ሆኜ እንዳገለግል ጠየቀኝ። ያ በ1953 ነበር።
ቴብል ቶክ፦ ዘ ናቪጌተርስ እነማን ናቸው? ተልእኳቸውስ ምንድን ነው? ዐብረኻቸውስ ምን ትሠራ ነበር?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ዘ ናቪጌተርስ በ1993 የጀመረ ሲሆን፣ በሎንግ ቢች በሚገኝ በአንድ የጦር መርከብ ላይ፣ ዳውሰን ትሮትማን የተባለ አንድ ሲቪል ግለ ሰብ፣ መርከበኛ የሆነ አንድ ሰውን ደቀ መዝሙር ማድረግ የጀመረበት ጊዜ ነበር። ያ መርከበኛም ሌላን ሰው ደቀ መዝሙር ማድረግ ጀመረ፤ ብዙም ሳይቈይ፣ መርከቧ ላይ በርካታ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። እምነታቸውን ለማካፈል በአካባቢዋ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን መጐብኘት ጀመሩ፤ ለቡድናቸውም ስም ማውጣትን ፈለጉ። እንደ መርከበኞች፣ ዘ ናቪጌተርስ የሚለውን ስያሜ መረጡ። በዛሬው ዕለት፣ ዘ ናቪጌተርስ ከወታደራዊ አገልግሎት ዐልፎ እጅግ የተስፋፋ ሲሆን፣ ከ30 ከሚበልጡ ብሔረ ሰቦች የተውጣጡ ከ4,000 የሚበልጡ ሰዎች፣ ከ100 በሚበልጡ አገራት ውስጥ ያገለግላሉ። ትኩረታችን፣ ተራው ሕዝብ በሚኖርበትና በሚሠራበት ቦታ ለሌሎች ሰዎች ወንጌልን እንዲሰብኩና ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ማሠልጠን፣ እንዲሁም የኮሌጅ ተማሪዎች በሌሎች ተማሪዎች መካከል ይህንኑ እንዲያደርጉ ማብቃት ነው።
በ1956፣ የመሥሪያ ቤቱ አስተዳዳሪዎች ክፍል አባል እንድሆን ተጠየቅሁ። በተለያዩ የአስተዳዳሪነት ኀላፊነቶች እስከ 1994 አገልግያለሁ። ነገር ግን፣ በ1986፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ መጻፍ ጀመርሁ። “ቅድስናን መከተል” የተሠኘው፣ የመጀመሪያው መጽሐፌ፣ በ1978 ታተመ። ራሴንም ጨምሮ ሁሉንም ሰው ያስገረመው ነገር፣ ምርጡ ተሸያጭ (best seller) መጽሐፍ መሆኑ ነው። በውጤቱም፣ ከናቪጌተርስ ውጭ ባሉ ጉባኤዎች እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት እንድናገር መጋበዝ ጀመርሁ። በቀጣዮቹ 15 ዓመታት፣ ከአስተዳዳሪነት ወደ ጸሓፊነትና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪነት ቀስ በቀስ ተዘዋወርሁ። ከ1997 ጀምሮ፣ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኮሌጅ አገልግሎት ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ አገልግያለሁ።
ቴብል ቶክ፦ የኮሌጅ ተማሪዎችን ስታገለግል፣ ከምንም በላይ ትርጒምና ደስታን የሚሰጥህ ምንድን ነው?
ጄሪ ብሪጅስ፦ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ክርስቶስን እንዲያመልኩ፣ እንዲታዘዙና እንዲያገለግሉ፣ እንዲሁም የተማሩትን ለሌሎች እንዲያስተላልፉ የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ ሥርዐትና ልማድ ሲያዳብሩ ማየት ነው። ባለፉት ዓመታት በተጓዝኩባቸው ጊዜያት የተገናኘኋቸውን፣ በኮሌጅ በነበሩበት ወቅት ከናቪጌተርስ ለተቀበሉት ደቀ መዝሙርነት አመስጋኝ መሆናቸውን የገለጹልኝን ሰዎች ብዛት ልነግርህ አልችልም።
ቴብል ቶክ፦ በአገልግሎት ዘመንህ በኮሌጅ ተማሪዎች ዘንድ ያስተዋልከው የተለመደው መንፈሳዊ ትግል ምንድን ነው? አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትስ ይህን ትግል እንዲያሸንፉ የኮሌጅ ተማሪዎችን እንዴት መርዳት ይችላሉ?
ጄሪ ብሪጅስ፦ የተለመደው መንፈሳዊ ትግል፣ በዓመታት ወስጥ በአስደናቂ ሁኔታ እንደ ተቀየረ ዐስባለሁ። ዛሬ፣ ትልቁ ትግል ከበይነ መረብ ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎች (internet pornography) ጋራ የሚደረገው ነው። ይህ ለሁሉም የወንድ ተማሪዎች እንዲሁም ለግማሹ የሴት ተማሪዎች በሚባል ደረጃ እውነት ነው። በይነ መረብ ብቻ ሳይሆን፣ በቴሌቪዥንና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ወሲባዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ምስሎች ያለማቋርጥ ጥቃት ያደርሱባቸዋል።
የበይነ መረብ ወሲብ ቀስቃሽ ምስልን የመመልከት ተሳትፎ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ከዐሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አከባቢ ላይ ነው፤ በመሆኑም፣ አብያተ ክርስቲያናት ሆኑ ወላጆች ይህን ጒዳይ በዋነኛነት ትኩረት ሰጥተው መፍታት ይኖርባቸዋል። እንዴት ወደሚለው ለመግባት ይህ ቦታው አይደለም፤ ግን የተለያዩ ግብአቶች አሉ።
ቴብል ቶክ፦ “በእግዚአብሔር መታመን” በተሠኘው መጽሐፍህ ላይ፣ በርካታ ክርስቲያኖች በመከራ ጊዜያት ውስጥ በእግዚአብሔር መታመን እንደሚከብዳቸው ገልጸሃል። በከባድ ጊዜያትም እንኳ፣ እግዚአብሔርን መታመን የምንማርባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው?
ጄሪ ብሪጅስ፦ በከባድ ወቅቶች እግዚአብሔርን መታመን፣ ሁሉንም የሕይወታችንን ክሥተቶችና ሁናቴዎች ፍጹም ይቈጣጠራል በማለት፣ ከሁሉ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ማመንን የሚያካትት ነው፡፡ በሁለተኛነት፣ እርሱ ሉዓላዊ በሆነው ልክ አፍቃሪም እንደ ሆነ ማመን አለብን፤ ይህም ለጥቅማችን የሚሆን ግብ የሌለውን ማንኛውንም ነገር ወደ ሕይወታችን እንዲገባ አይፈቅድም የሚለውን ይመለከታል። በእነዚህ ከባድ ወቅቶች መኻል፣ እርሱ ከቶውኑ እንደማይተወን ወይም እንደማይጥለን ማመንንም ያካትታል። ምንም እንኳ እነዚህ ዋና ዋና ነጥቦች ቢሆኑም፣ የእግዚአብሔር መንገዶች ብዙውን ጊዜ ምስጢራዊና የማይመረመሩ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን፤ ስለ ሆነም በማንረዳቸው ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ በርሱ እንድንታመን ተጠርተናል።
ቴብል ቶክ፦ ክርስቲያኖች በክርስቶስ በኩል ጻድቅ ሆነው ከተቈጠሩ፣ ግላዊ ቅድስናን መከታተል ለምን ያስፈልጋቸዋል?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ለዚህ ጥያቄ ዐጭሩ መልስ የሚሆነው፣ እግዚአብሔር ስላዘዘው ነው፤ በ1ጴጥሮስ 1፥16፣ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሏልና። ነገር ግን እግዚአብሔር ማድረግ ያለብንን ነገር እንድናደርግ ይፈልጋል፤ እንዲሁም ማድረግ ያለብንን ነገር እንድናደርግ ሊያነሣሣን የሚገባው፣ በክርስቶስ አማካይነት ኀጢአታችንን ይቅር በማለትና የራሱን የክርስቶስን ፍጹም ጽድቅ በመስጠት ላደረገልን ነገር ያለን አመስጋኝነት ነው።
ቴብል ቶክ፦ “ጸጋን የመቀበያ መሣሪያዎች” ምንድን ናቸው?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ጸጋ የመቀበያ መሣሪያዎች እግዚአብሔር ለእኛ ጥቅም የሰጠን ግላዊና መንፈሳዊ የሆኑ ሥርዐቶችና ልምምዶች ናቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ጋራ በየዕለቱ ለብቻችን የምናሳልፈውን ጊዜ፣ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቃል መያዝና ጸሎትን ያካትታሉ። በተጨማሪም ዐብሮ ማምለክ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ማዳመጥና የቤተ ክርስቲያን ሥርዐቶችን (sacraments) መካፈል የተሠኙት የማኅበር ሥርዐቶችና መንፈሳዊ ልምምዶችም ናቸው።
ቴብል ቶክ፦ ግላዊ የሆነ መንፈሳዊ ልምምድ (discipline) የሞላበት ኑሮ ጸጋን ይቃወማል ብለው ብዙዎች ያስባሉ። ይህ እውነት ነውን? ካልሆነስ፣ ለምን?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ግላዊ የሆነ መንፈሳዊ ልምምድ ጸጋን እንደሚቃወም ብዙዎች የሚያስቡበት ምክንያት፣ የእነዚህ ሥርዐቶች ልምምድ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ያስገኝልናል ብለው ስለሚያስቡ ነው። ግላዊ ሥርዐት ጸጋን የሚቃወም አይደለም። ይልቁንስ፣ አንድ ሰው በጥሩ ሁኔታ እንደ ገለጸው፣ ጸጋ የግላዊ ሥርዐቶችን አስፈልጎት አያስወግድም፤ ይልቁንስ ውጤታማ ያደርጋቸዋል።
ቴብል ቶክ፦ “የተከበሩ ኀጢአቶች” በተሠኘው መጽሐፍህ ላይ፣ ኀጢአቶችን እርስ በእርስ በማነጻጸር፣ አንዳንዶቹ በእግዚአብሔር ዘንድ ኢምንት እንደሆኑ በማሰባችን ምክንያት፣ እኛ ክርስቲያኖች በአብዛኛው ችላ ስለምንላቸው በርካታ ኀጢአቶች ተናግረሃል። በመጽሐፍህ ከጠቀስሃቸው ባሻገር፣ ክርስቲያኖች የሚሠሯቸው “የተከበሩ ኀጢአቶች” ምንድን ናቸው?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ክርስቲያኖች ከሚሠሯቸው በጣም ከተለመዱ ኀጢአቶች መኻል አንዱ፣ በመከራ መኻል የእግዚአብሔርን ፍቅር መጠራጠር ነው። “እግዚአብሔር የእውነትም ቢወድደኝ ኖሮ፣ ይህ እንዲሆንብኝ አይፈቅድም ነበር።” ብለን እናስባለን፡፡ ሌሎች የተከበሩ ኀጢአቶች እንደ ርኅራኄ፣ ትሕትና፣ ደግነት፣ ቸርነትና ደስታ የመሳሰሉትን አዎንታዊ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማሳየት አለመቻል በሚለው ምድብ ውስጥ እንደሚወድቁ ዐስባለሁ። የእነዚህ ባሕርያት የተሟላ ዝርዝር በገላትያ 5፥22-23 እና በቈላስይስ 3፥12-14 ላይ ይገኛል።
ቴብል ቶክ፦ ቅድስናን ስለ መከተል በደንብ ያስተማረህ መምህር የትኛው ነው? እናም ለምን?
ጄሪ ብሪጅስ፦ ፒውሪታኑ የሥነ መለኮት ሰው ጆን ኦወን፣ በመጻሕፍቱ በኩል፣ መካሪዬ ሆኗል፤ እንዲሁም ቅድስናን ስለ መከታተል ብዙ አስተምሮኛል። “ፈተና እና ኀጢአት” የተሠኘው፣ በኀጢአት ላይ የተጻፉ ሦስት የድርሰቶችን (treatises) ስብስብ ያካተተው መጽሐፉ፣ “በገዛ ራስህ ጣር” እና “በእኔ በኩል ኢየሱስ ሕይወቱን እንዲኖር ብቻ ልፍቀድ” የሚሉትን ሁለት ጽንፎች እንዳስወግድ ረድቶኛል።
ቴብል ቶክ፦ በአገልግሎት ዘመንህ እግዚአብሔር ካስተማረህ ወሳኝ ትምህርቶች መካከል የተወሰነትን ብትነግረን?
ጄሪ ብሪጅስ፦ እነርሱን በተማርኩበት ቅደም ተከተል ዕንኾ፦
የመጀመሪያው የሚሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ማለትም መመሪያዎቹና ተስፋዎቹ፣ በሕይወታችን ውስጥ ለሚገጥሙን የተወሰኑ ሁኔታዎች ተግባራዊ እንድናደርጋቸው የታሰቡ ናቸው።
ሁለተኛው፣ ከክርስቶስ ጋራ ያለን አንድነት ጥቅም ሲሆን፣ ይህም በሕይወቱና በሞቱ በእግዚአብሔር ፊት ወኪላችን መሆኑና ከዚያም ኢየሱስ በዮሐንስ 15 ላይ ባለው የወይን ተክልና ቅርንጫፎች ምሳሌ እንዳስተማረን የመንፈሳዊ ሕይወታችን ምንጭ መሆኑ ነው።
ሦስተኛው ደግሞ፣ ቅድስናን መከተል ትጋት የተሞላው ጥረታችንን ያካትታል፤ ነገር ግን እነዚህን ጥረቶች እንዲባርክ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ጥገኛ መሆን አለብን።
አራተኛው፣ በድነታችን ላይ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ምርጫ አስተምህሮ መረዳቴና መቀበሌ ነው። ይህ ምናልባትም ከሁሉም ትምህርቶች በላቀ ሕይወቴን የቀየረው ነው።
ዐምስተኛው፣ ወንጌሉ የሚያስፈልገው፣ የማያምኑት ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እኛ አማኞች አሁንም ኀጢአተኞች ስለ ሆንን በየዕለቱ ወንጌሉ ያስፈልገናል።
ስድስተኛው፣ የክርስቶስ ሥራ በእኛ እንዲተገበርና በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ እንድናድግ የሚያስችለንን በውስጣችን የሚኖረውን የመንፈስ ቅዱስን ሚና የበለጠ መረዳት ነው።