ሐዘንተኛ ሆኖ ደስተኛ | ሕዳር 26

አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።” (ዘዳግም 7፥6)

ከመዳናችን ጀርባ ያለው የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት በአምስቱ የጸጋ አስተምህሮ ነጥቦች ይብራራል። እነዚህ ነጥቦች የጆን ካልቪንን እና የበርካታ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የድነት አስተምህሮ በአጭሩ የምናስቀምጥበት ነጥቦች ናቸው። ታዲያ እነዚህን አስተምህሮዎች የቤተ ክርስቲያን አባት የሚባለው አውገስጢኖስ ደስታ እና እርካታን በሚረዳበት መንገድ ብናብራራቸው ምን ሊመስሉ ይችሉ ይሆን?

አጠቃላይ ውድቀት፦ በሚለው ነጥብ ውስጥ ርኩሰታችን ክፋት ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ውበት መታወር እና ለጥልቅ ደስታ መሞት እንደሆነ እንረዳለን።

ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ፦ ይህ ማለት ከመፈጠራችን በፊት ደስታችን በኢየሱስ ፍጹም እንዲሆን ታቅዶልን እንደነበር እና ይህም ደስታ በሥላሴ አንድነት ውስጥ ከሚፈሰው ከእግዚአብሔር ደስታ ጋር አብሮ ያለ እንደሆነ እንረዳለን።

የተገደበ ሥርየት፦ በሚለው ውስጥ ደግሞ የእግዚአብሔር ህዝብ በአምላኩ ላይ የተመሠረተ የማይናወጥ ደስታ እንዲኖረው የአዲሱ ኪዳን ደም ለዘላለም ላይሻር አረጋግጦለታል የሚለውን እንረዳለን።

የሚያሸንፍ ጸጋ፦ ማለት ራሳችንን በሚያጠፉ ጊዜያዊ ተድላዎች ከመታሰር ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ጉልበት እና ቁርጠኝነት ከዓለም እጅግ በሚልቅ እርካታ በሉዓላዊ ኅይሉ ልጆቹን ነፃ የሚያወጣበት ጸጋው ነው።

የቅዱሳን መጽናት፦ ማለት ኅያሉ እግዚአብሔር ወደ ርካሽ ተድላዎች ወድቀን እንዳጠፋ እየጠበቀ፣ በሚልቁ እግዚአብሔራዊ ደስታዎች አጥብቆ የሚይዝበት ማጽናቱ ነው። በመከራ እና በስቃይ መካከል እያሳለፈ፣ በቀኙ ላለ ፍሰሐ እና በፊቱ ላለው የዘላለም ተድላ ያበቃናል ማለት ነው።

ከእነዚህ ከአምስቱ ነጥቦች፣ ቅድመ ሁኔታ የሌለው ምርጫ የሚለው ለነፍሴ ከሚከብዱኝ እና ከሚጣፍጡኝ እውነቶች ዋነኛው ነው። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ራሴን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳልችል ይሰብረኛል። ይህ ከባዱ ሐቅ ነው። ምርጫ መሆኑ ደግሞ የእግዚአብሔር ውድ ሀብቱ ያደርገኛል፤ ይህ ደግሞ እጅግ ጣፋጭ እውነት ነው።

ይህ ከጸጋ ትምህርት ብዙ ውበቶች ውስጥ አንዱ ነው፦ ተስፋ አስቆራጮቹ መርዶዎች ለታላቅ ደስታ ያዘጋጁናል።

መመረጣችን የእኛ ስራ ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ፣ “አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ” (ዘዳግም 7፥6) የሚለውን ስናነብ ምነኛ እንታበይ ነበር። ነገር ግን እኛን ከኩራት ለመጠበቅ፣ የተመረጥነው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ጌታ ያስተምረናል (ዘዳግም 7፥7–9)። ምስኪኑን ሀብቱ በማድረጉ በደስታ እናዜማለን።

የሚመርጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ቅድመ ሁኔታ የሌለው እና ነፃ መሆኑ፣ ለራሳችን አንዳች ክብር ሳንሰጥ ይህን ውድ የሆነ ስጦታ ወስደን እንድናጣጥም ያደርገናል።