“ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና። (ማቴዎስ 5፥11–12)
እንደ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ ለመደሰት የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ ክርስቲያን ሄዶኒዝም ያስተምራል። እነዚህ ሁሉ መንገዶች ሁሉን ቻይ የሆነውንና ፍጹም እርካታ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ሊሆኑ ይገባል።
በመከራ ውስጥ የምንደሰትበት አንዱ መንገድ፣ በትንሣኤ በምናገኘው ሽልማት ታላቅነት ላይ አእምሯችንን በአንክሮ በመትከል ነው። የዚህ ዐይነቱ ትኩረት ውጤት፣ አሁን ያለው ሥቃያችን ከሚመጣው ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳልሆነ እንድንረዳ ማድረግ ነው፦ “የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ” ብሏል ጳውሎስ (ሮሜ 8፥18፣ 2 ቆሮንቶስ 4፥16–18)። ሊገለጥ ባለው ሽልማታችን መደሰት መከራውን እንድንታገሰው ከማድረግ ባለፈ፣ በፍቅር እንድንኖር ያስችለናል።
“ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል” (ሉቃስ 6፥35)። ለድሆች ለጋስ ሁን፤ በዚህ “ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል” ይላል ሉቃስ 14፥14። በዚህ ቃል በተገባ ብድራት መታመን፣ የዓለማዊነትን ገመድ ይበጥሳል፣ ለፍቅርም ለሚከፈል ዋጋ ነፃ ያደርገናል።
በመከራ ውስጥ የምንደሰትበት ሌላው መንገድ፣ መከራ በተስፋ ማረጋገጫችን ላይ ካስከተለው ውጤት የሚመጣ ነው። በመከራ ውስጥ ያለው ደስታ የተመሰረተው በትንሣኤ ተስፋና በዋጋው ላይ ብቻ አይደለም፤ ይልቅ መከራው ራሱ ይህን ተስፋ ለማጠናከር በሚሠራበት መንገድ ላይ ጭምር እንጂ።
ለምሳሌ፣ ጳውሎስ፦ “በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን” ብሏል (ሮሜ 5፥3-4)።
በሌላ አነጋገር፣ የጳውሎስ ደስታ የተመሰረተው በታላቅ ብድራቱ ላይ ብቻ አይደለም፤ ይልቅ የብድራቱን ተስፋ በሚያጠናክረው በመከራው ውጤት ላይም እንጂ። መከራ ትዕግሥትን ያስገኛል፤ ትዕግስት ደግሞ እምነታችን እውነተኛ እና ከልብ የመነጨ የመሆኑን ስሜት ይፈጥራል፣ ይህም ክርስቶስን እንደምናገኝ ያለንን ተስፋ ያጠናክርልናል።
ስለዚህ ትኩረታችን በብድራቱ ባለጠግነትም ላይ ሆነ በመከራው የማንጻት አቅም ላይ፣ የእግዚአብሔር ዓላማ በመከራ ውስጥ ያለው ደስታችን የተጠበቀ እና የጸና እንዲሆን ማድረግ ነው።