ጥላዎቹን መተካት | ታሕሳስ 16

እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው።

ዕብራውያን 8፥1-2

የዕብራውያን መጽሐፍ ዋና ነጥብ፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው የመጨረሻውና ምርጡ ሊቀ ካህናት በመሆን ምድራዊውን የሊቀ ካህናት አገልግሎት ለመፈጸም ብቻ አለመሆኑን ማሳየት ነው። ይልቁኑም፤ ያንን አሠራር ራሱ ፈጽሞ በቃ ሊል፣ ትኩረታችንንም ሁሉ ወደ ራሱ ሊያዞር እና፣ በቀራንዮ የመጨረሻው መሥዋዕታችን በመሆን የጀመረውን አገልግሎቱን በመንግሥተ ሰማይ የመጨረሻው ሊቀ ካህናታችን በመሆን ሊፈጽም እንደሆነ ማብሰር ነው።

የብሉይ ኪዳን መገናኛ ድንኳን፣ ካህናት፣ እና መሥዋዕት ሁሉ ለሚመጣው እውነታ ጥላዎች ነበሩ። አሁን ፍጹም የሆነው እውነታ መጥቷል፤ እነርሱም አልፈዋል።

ለልጆች እና ልጆች ለነበሩ ሁሉ የሚሆን የገና በዓል ምሳሌ ልስጣችሁ። ከእናታችሁ ጋር ሰፊ ገበያ ሄዳችሁ ድንገት ሳታስቡት ብትጠፋፉ ብላችሁ አስቡ። በፍርሀት እና በድንጋጤ ሆናችሁ፣ የምትሄዱበት ጠፍቷችሁ ማልቀስ ልትጀምሩ ስትሉ፣ ከሆነ ግድግዳ ጀርባ የእናታችሁን የሚመስል ጥላ ድንገት መሬቱ ላይ ብታዩ በቅጽበት ተስፋ ታደርጋላችሁ። ግን የቱ ይሻላል? ጥላ በማየት የሚሰነቅ ተስፋ፣ ወይስ ራሷ እናታችሁ ከተሸፈነችበት ብቅ ስትል ያለው ስሜት?

ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን ሊሆን ሲመጣ ያለውም ስሜት ልክ እንዲሁ ነው። የገና በዓል ማለት ይህ ነው። ገና ማለት ጥላ የነበረው ሥርዓት በትክክለኛው ማንነት ሲተካ ማለት ነው። እናቱ የጠፋችበት ሕፃን ከተከለለችበት ግድግዳ ብቅ ስትል የሚሰማው የእፎይታ እና የደስታ ስሜት።

(ኢየሱስ ብሉይ ኪዳንን እንዴት እንደተካው ተጨማሪ ለማንበብ፣ በዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ያለውን ዐባሪ ይመልከቱ።)