ዕጣ በጒያ ውስጥ ይጣላል፤ ውሳኔው በሙሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (ምሳሌ 16፥33)።
የትኛውም ዕጣ ሲወጣ፣ ዕልፍ ጊዜ በዘፈቀደ እንዲሆን በከረጢት ውስጥ ቢዘበራረቅ፣ የዕጣው ውጤት የሚወሰነው በእግዚአብሔር እንደሆነ ይህ ጥቅስ ይነግረናል።
በሌላ አባባል እግዚአብሔር ለዕቅዱ የማይጠቀምበት ምንም አይነት ጥቃቅን ክስተት የለም። ኢየሱስም “በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም” ብሏል (ማቴዎስ 10፥29-30)።
በቁማር ቤት ውስጥ የሚወረወረው እያንዳንዱ ጠጠር ውጤት፣ በሺህ ጫካዎች ውስጥ የሚሞቱት ትናንሽ ወፎች ሳይቀሩ፣ እያንዳንዳቸው በእግዚአብሔር ሉዓላዊ እቅድና ትእዛዝ ውስጥ ናቸው።
በትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ላይ የተጣለው ዕጣ በዮናስ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን። እግዚአብሔር አንድ አሳ ዮናስን እንዲውጠው ትዕዛዝ ይሰጣል (ዮናስ 1፥17)፤ ጥላ የሚሆንለት ተክል እንዲበቅል ያዛል (4፥6)፤ ደግሞም ተክሉን እንዲገድለው ትልን ያዛል (4፥7)።
ከአሳ እና ከትላትል ሕይወት ከፍ ባለ ሁኔታ ደግሞ፣ ከዋክብት በስፍራቸውና በቦታቸው ላይ የሚቀመጡት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው።
ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም (ኢሳይያስ 40፥26)።
ይህንን ሁሉ የሚቆጣጠር እግዚአብሔር፣ በተፈጥሮና በሕይወት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው። የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በሽታ እና አካል ጉዳቶች፣ አልፎም ሞት ድረስ ያለውን የዚህን ዓለም የተፈጥሮ ክስተት ያለ አንዳች ስሕተት በክንዱ ይገዛል።
ከዋክብት ሚዞሩት በምሕዋራቸው
ሚኖሩት ሚሞቱት በሕጉ አዟቸው
ፀሐይ ባለችበት በምድቧ ቦታ
ታዛ ታበራለች በአምላክ እርዳታ
ኮረብታ፣ ተራሮች፣ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች
ክብሩን ያውጃሉ የውቅያኖስ ጥልቆች።
(“Let All Things Now Living,” ካትሪን ዴቪስ)
ስለዚህ የትኛውም የተፈጥሮ ክስተት ከእግዚአብሔር ጥበብ፣ መልካም እቅድና ፍጹም ቁጥጥር ውጪ እንዳልሆነ በማወቅ፣ በመደነቅና በአክብሮት በሰላምም እንኑር።