እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል (1ኛ ጴጥሮስ 4፥1)።
ይህ ጥቅስ መጀመሪያ ግራ ያጋባል። ክርስቶስ ኅጢአትን መተው ነበረበት? በፍጹም! “እርሱ ኀጢአት አላደረገም” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥22)።
ከዚያ ግን ግልጽ ይሆናል። ክርስቶስ ለእኛ ሲል እንደተሰቃየ ስናስብ፣ ከእርሱ ጋር መሞታችን ግልጽ ይሆንልናል። “ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥24)። ከእርሱ ጋር ስንሞት ደግሞ፣ ኅጢአት መሥራትን እናቆማለን።
ሮሜ 6፥6-7፣ 11 እንዲህ ይላል፦ “ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር ወይም ኀይል እንዳይኖረው አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነፃ ወጥቶአል።… እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቊጠሩ።”
ጴጥሮስ “በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ” ይላል!
ጳውሎስ ደግሞ “እንደሞታችሁ አስቡ” ይላል!
ከኅጢአት ጋር ለምናደርገው ውግያ መሣሪያችን ይህ አስተሳሰብ ነው።
ውሸት፣ ምኞት፣ ቅናት፣ ስርቆት፣ በቀል እና የመሳሰሉ የሰይጣን ፈተናዎች በደጃችሁ ሲያደቡ፣ በዚህ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡባቸው፦ አምላኬ እኔን ከኅጢአት ለማዳን ሲሠቃይ እና ሲሞት፣ እኔም ለኅጢአት ሞቻለሁ!
ሰይጣን በጆሮህ ወይም በጆሮሽ መጥቶ፣ “ለምን የሴሰኝነት ምኞትህን ትከለክላለህ?” ወይም፣ “ለምን ቶሎ ዋሽተሽ ከዚህ ጭንቅንቅ ውስጥ አትወጪም?”፣ “ለምን ያቺን ስትመኚያት የነበረውን ምርጥ የቅንጦት ዕቃ አትገዢያትም?”፣ “ለምን የበደለህን ሰውዬ ተበቅለህ ፍትሕ አታገኝም?” ሲልህ ወይም ሲልሽ …
ይህን መልሱለት፦ “የእግዚአብሔር ልጅ እኔን ከኅጢአት ለማዳን ሲል በእጅጉ ተሰቃይቷል፣ የምር ተሰቃይቷል፤ ይሄ ሁሉ ሥቃይ ደግሞ የወረደበት እኔን የሚያማርር ነገር ውስጥ ሊከተኝ አይደለም፤ እርሱ በሞቱ የገዛልኝ ዘለዓለማዊ ደስታ በኅጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ሁሉ የሚበልጥ ነገር ነው። የእርሱ የጽድቅ ተስፋ ካንተ የኀጢአት ተስፋ ይበልጣል። አምነዋለሁ፣ እርሱን ስለማምነው ለማታለያዎችህ አልወድቅም። ከረሜላህን ይዘህ ከፊቴ ጥፋ! ከእንግዲህ በከረሜላ ፋብሪካህ አጠገብ ሳልፍ ላንተ ከንቱ ተስፋ ለኀጬ አይዝረከረክም።”